መለመድ ከሌለባቸው ተግባራት መካከል ነው። “አስር ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ” እንደሚባለው አይነት ውሳኔን ይፈልጋል። መፍረስ ያለበትን ማፍረስ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው። መፍረስ የሌለበትን ማፍረስ ደግሞ የመብት ጉዳይ ሳይሆን የሕግ ጥሰት ነው። በዚህ የተነሳም ተግባሩ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ይፈልጋል።
ሕገወጥ ግንባታም እንደዛው ነው። ሕገወጥ የሚሆነው ግንባታው ብቻ ሳይሆን ገንቢውም ነው፤ ሕገወጥ የሚሆነው ገዥም ሻጭም ነው፤ ይህም ልክ እንደ ማፍረስ ሁሉ የራሱ የሆነ ዲሲፕሊን አለው፤ ለሕግ ተገዥነትን ይፈልጋል።
አሁን ላይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ”ሕገወጥ ግንባታዎችን” የማፍረስ ስራ በስፋት ሲከናወን ይታያል። ይህ ፀሀፊ ከአፍራሹም ከሚፈርስባቸውም ወገኖች ስላልሆነ በጉዳዩ ላይ ጥርት ያለ መረጃ/ግንዛቤ የለውም። በመሆኑም እንደ ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ወደ ፊት መሆን ያለበት ላይ ብቻ በማተኮር አንዳንድ ሀሳቦችን ለመሰንዘር ይሞክራል።
በመሰረቱ፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋን ሳይጨምር፣ አንድ ነገር እንዲፈርስ ሲፈለግ ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ይችላል። ወይ ሕገወጥ ስለሆነ፣ አልያም ስፍራው ለሌላ፣ ለተሻለ ነገር (ግንባታ) ስለተፈለገ፤ ወይም ሌላም ሌላም ሊሆን ይችላል (መቸም “ያይንህ ቀለም ስላላማረኝ” ሊሆን አይችልም)።
ብቻ ምንም ይሁን ምን ጉዳዩ በቀጥታ ከሰው ጋር የተያያዘ ነውና ያንን አስቦ መስራት (መገንባቱም ሆነ ማፍረሱ) ተገቢ ይሆናል። አሁን ለጊዜው እየፈረሱ ያሉት ፈራሾች ሕገ ወጥ ስለሆኑ ነው እንበል፤ አልያም ለተሻለ ልማት ስለተፈለጉ ነው እንበል።
እዚህ ላይ በግልጽ የሚስተዋለው፤ የማፍረሱ ተግባር በምንም፣ ምክንያት ይከናወን፤ ለብዙዎች አጀንዳ ሆኗል / ለአገር ደግ ለሚያስቡት ጭምር/። በመሆኑም ይህ አይነቱ ፈተና እንዳይደገም ከተፈለገ እራሱ “ማፍረስ”ም መደገም እንዳይኖርበት አሁን ላይ ቆመን ማሰብ ይኖርብናል።
ለምሳሌ በሸገር አካባቢ እየፈረሱ ያሉት ፈራሾች የተሰጣቸው ስያሜ “ሕገወጥ”ነት ነው። እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በሕገ ወጥነት (በተለይ ወደ አስፋልት ገፍቶ በመስራት፤ ባዶ ቦታን ሁሉ የመጠቀም ተግባር) እየፈረሱ ያሉት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ምንም ሆነ ምን ግን ኢኮኖሚው ያገር ነውና ጉዳዩ ቢያነጋግር አይገርምም።
ሕገወጥነትን ለመከላከል መሳሪያው ሕግ እና ሕጋዊነት ናቸው። ሌላ ካለ አላውቅም። በመሆኑም የሕግ የበላይነት በሚከበርበት አገር ሕገወጥነት አይኖርም ማለት ይሆናል። ያ ማለት ደግሞ ሕገወጥነትን ተከትለው የሚመጡ ተግባራት በሙሉ አይመጡም ማለት ነው፣ በተራዛሚው የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም ሆኑ የአገር ሀብት ምዝበራ፤ ወይም ማህበራዊ ተመሰቃቅሎ አይኖርም ማለት ይሆናል።
ይህ ዝም ብለን በገደምዳሜው እየገለፅነው ያለው ጉዳይ እባለቤቱ ቦታ ሆኖ ለተመለከተው ምናልባት ጉዳዩ መራር ይሆናል። እዚህ ማለት የተፈለገው “ችግሩ በዙር እንዳይደገም ምን መደረግ አለበት?” የሚለውን አንስቶ ሀሳብ መለዋወጥ ነው።
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት የማያውቀው መሬት የለም። ያ ማለት፣ መንግሥት የማያስተዳድረው መሬት የለም ማለት ነው። እያንዳንዷ የመሬት አካል ቢያንስ ቀበሌ ያውቃታል ማለት ነው፣ ከዚህ የተነሳም ሕገወጥ ግንባታ በስፋት ሊኖር የሚችልበት እድል ጠባብ ነው። ይህ ካልሆነ ሕገወጡን ከሕጋዊው መለየት ያስቸግራልና በዚህ ላይ መሰራት አለበት።
እንዴት መንግስት ባለበት አገር አንድ ከተማን የሚያክል ግንባታ ይካሄዳል? እንዴት ሕገወጥ ለሆነ ግንባታስ ሁሉ ነገር እንዲሟላለትና ከሕጋውያኑ በላይ ሕጋዊ እስኪመስል ድረስ አገልግሎትን ያገኛል? እንዴትስ ሕጋዊ አለመሆኑ እየታወቀ አስርት ዓመታትን በኢ- ሕጋዊነት ሊኖር ይችላል? ወዘተርፈ የሚሉ ጥያቄዎችን በአግባቡ ማየትና መልሳቸውን በአግባቡ ማጤን፤ ለችግሮቹም ባለቤት መስጠት ተገቢ ነው።
ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሚደረግን ማፍረስ ማንም አይቃወምም። ለምሳሌ እዚህ አሁን እኔ ቁጭ ብዬ የምፅፍበት ስፍራ ለትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መንገድ . . . ከተፈለገ “እኔ ወዴት ልሂድ?” እንጂ፣ ከቆምኩበት አልንቀሳቀስም ማለት አይገባኝም። ምናልባት ጥያቄው ሊሆን የሚችለው የፈረሰበት አካል ከፈረሰበት በኋላ የሚኖረው ሁኔታና የሰብአዊ መብቱ ይዞታ ነው። ያ ደግሞ የግድ ነውና “ለምን?” አያሰኝም።
የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ አላማና አነሳስ “አሁን እየታየ ያለው የማፍረስ ተግባር ዳግም ተመልሶ እንዳይከሰት ምን ይደረግ?” የሚለውን ማስረፅ ነው። በመሆኑም፣ ሁሉም ሰው በሕግ እና ሕጋዊነት ላይ ብቻ በመመስረት ስራውን ይስራ። ሁሉም አካል ከማንኛውም ውገና፣ ከማንኛውም ሙስና፣ ከማንኛው አድልኦ፣ ከማንኛውም . . . ከማንኛውም . . . ይፅዳ።
መሸጥም ሆነ መለወጥ ሕጋዊ ይሁን፤ መገንባትም ሆነ ማፍረስ ሕጋዊ ይሁን፤ ሕገወጥነትን በሕግና ሕጋዊነት በእንጭጩ እናስቀር፤ በእቅድ መመራትን ባህላችን እናድርግ። እኩል ተጠያቂነት ይስፈን፤ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሰው ተኮር ይሁኑ።
የተቋማት ሚና “ይህ ሕገወጥ ነውና አይሰራም” በማለት ከጅምሩ ማስቆም ላይ ሊሆን እንጂ፣ ሲሰራ ዳር ቆሞ መመልከት፤ ካለቀ በኋላ “ሕገወጥ ነውና ይፍረስ” ማለት ላይ መሆን የለበትም። እነዚህን ሁሉ ካላደረግንና “ማፍረስ እንዳይደገም” በቁርጠኝነት ካልሰራን ውሀ ቢወቅጡት እምቦጭ ነውና የዜጎች ሕይወት እንደ ተጎሳቆለ ይኖር ዘንድ ይገደዳል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም