አዲስ አበባ:- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞንና በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ ተከስቶ የነበረው ግጭት ማህበረሰቡን ለማረጋጋት የሁለቱ ክልሎችና የፌዴራል መንግ ሥት የፀጥታ አካላት እየሰሩ መሆኑ ተገለጸ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግል ገል በለስ እና ዳንጉር አቅራቢያዎች ላይ የተከሰተው ግጭት እንዳይቀጥል የማረጋጋት እና ህዝብን ከህዝብ ጋር የማወያየት ተግባር በመፈፀሙ የአካባቢውን ሰላም ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ገለታ ሃይሌ በተለይ ለአዲስ ዘመን ትናንት እንደገለፁት፤ አማራ ክልል ጋር በመተባበር የሁለቱም ክልል አመራሮች ግጭቱ በተነሳበት አካባቢ ተገኝተው ማህበረሰቡን የማረጋጋት ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ። የተጀመረው እንዳይቀጥል እና ወደ ፊትም ተመሳ ሳይ ጉዳት እንዳይከሰት ህዝብን የማወያየት ሥራ እየተሰራ ነው።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተጨማሪ ከሚያዝያ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ጃዊ አካባቢም ከባድ ግጭት እንደነበር ተናግረው፤ በአካባቢው የሚገኙ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እየሰሩ በመሆኑ አሁን የተሻለ መረጋጋት ተፈጥሯል። በቀጣይ ህዝቡ ግጭት ፈጣሪዎችን የማጋለጥ ሥራ ከሰራ እና ከመንግሥት ጋራ ከተባበረ በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚቻልና አስተማማኝ ሰላም እንደሚሰፍንም አብራርተዋል።
ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የምር መራ ቡድን ወደ ቦታው ማቅናቱን ጠቁመው፤ በጃዊ የደረሰው ከባድ እንደነበር በመጥቀስ፤ የጉዳቱ መጠን ወደ ፊት የሚገለፅ ይሆናል ብለዋል። ነገር ግን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሁለት ቀበሌ ህዝብ የተፈናቀለ ሲሆን፤ ዳንጉራ አካባቢ አይስካ ቀበሌ የ21 ሰው ህይወት እንደጠፋ እና 80 ሰው ጉዳት ደርሶበት ፓዊ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተሰጠው መሆ ኑን ጠቁመዋል።
በአማራ ክልላዊ መንግሥት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ አሰማኸኝ አስረስ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ጠቡ እየሰፋ ሄዶ ጉዳት ደርሷል።
ሆኖም ከመጋቢት 18 ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊሲ እንዲሁም የሁለቱም ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ግጭቱ ወደ ተከሰተባቸው ቦታዎች በመሄድ ከፍተኛ ሥራ አከናውነዋል። አሁንም በመስራት ላይ ሲሆኑ፤ በአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት ሰፍኗል ብለዋል።
መረጃዎችን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በየጊዜው በማሰራጨት ጉዳዩ እንዳይሰፋ እና መረጋጋት እንዲፈጠር ከመስራት በተጨማሪ፤ ከአካባቢው ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት በማድረግ የማረጋጋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሁለቱም ክልሎች የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች የሁለቱንም ክልሎች በጥልቀት በመመርመር የግጭቶቹን ሪፖርት እንዲያቀርቡ፤ በተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ ባሉበት የመፍትሄ ሃሳብ አፍልቀው ችግሮችን እንዲፈቱ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ወደ አማራ ክልል ጃዊ ወረዳ አንድ ቡድን ተንቀሳቅሶ አሁንም እያጣራ መሆኑን ተናግረዋል።
የፌዴራል መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊሲ እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ባደረገው የተቀናጀ ርብርብ ስጋት የለም ባይባልም ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ አካባቢዎች ወደ ሰላም እና መረጋጋት መግባታቸውንም አቶ አሰማኸኝ ተናግረዋል።
‹‹በጃዊ የተከሰተው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተፈጠረው ግጭት የተቆጡ ሰዎች ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ ›› ካሉ በኋላ፤ ይህንን የማጣራት ተግባር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ከሁለቱም ብሔረሰብ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች መኖራቸውን በመጠቆም፤ ጉዳዩ አሳዛኝ እና አሳፋሪ ነው ብለዋል።
የደረሰው ጉዳት መጠኑ እየተጣራ መሆኑን ገልፀው፤ መረጃው በትክክል ተጠቃሎ እንደደረሰ እንደሚገለጽ ጠቁመዋል። ከሁለቱም ክልል የፀጥታ ኃይል የተውጣጣ ኮሚቴ በጋራ እየሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
በምህረት ሞገስ