ማህበራቸውን “ሴቶች ይችላሉ” ብሎ ለመሰየም ያበቃቸው ብዙ ቢኖራቸውም የፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ አዘጋጅ ሆነው በኖርዌጅያን የወሰዱት ስልጠና ዋናው ነው፡፡ ሰው የየራሱ መክሊት አለው እንደሚባለው ሁሉ ኖርዌጂያን ደግሞ ሴቶች የራሳቸው ዕውቀት አላቸው ይላሉ፡፡ የ‹ሴቶች ይችላሉ›› ማህበር መስራችና ዋና ዳይሬክተር ደራሲና ጋዜጠኛ የምወድሽ በቀለ ይሄን የኖርዌጅያኑን ሴቶች ይችላሉ አስተሳሰብ በውስጣቸው ይዘው ነው የቆዩት፡፡ ኖርዌጅያኑ ሴቶች ይችላሉ ብለው የሚያምኑበትን አስተሳሰባቸውን እራሳቸውም ከሚያዩት፤ ከሚሰሙትና ከሚያነቡት ከውጤቱም እያከሉ ዕውነትነቱን ሲያረጋግጡም ቆይተዋል፡፡
ብዙ ቤተሰብ ውስጥ አባ ወራው ቤቱን ያስተዳድራል ይባል እንጂ እሱ የሚሰጠውን ወጪ እየቆጠቡ ከወር እስከ ወር ቤተሰብን፤ በተለይም ልጆችን የመመገብ፤ የመንከባከብ፤ ሌሎች ማህበራዊ ኃላፊነቶችን የመወጣት ተግባር ሙሉ፤ በሙሉ በሚባልበት ሁኔታ የሴቶች ድርሻ የመሆኑን ጉዳይ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ሲታዘቡ መኖራቸው አንዱ ነው፡፡
‹‹ማልደው የሚነሱትም ሆነ አምሽተው የሚተኙት ሴቶች ናቸው›› የሚሉት ዳይሬክተሯ ወንዶች ይሄን የሴቷን ያህል ሸክም መሸከም እንደማይችሉ ይጠቁማሉ፡፡ ፈጣሪ ከባዱን እርግዝና እና ምጥ በመቻል የሰው ልጆችን ሕይወት የማስቀጠሉን ኃላፊነት ለሴቷ ሊሰጥ የቻለበት ምክንያትም ይሄው እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ በሥራ ፀባያቸውም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች ታች ያለችውንና የትምህርት ደጃፍ እንኳን ያረገጠችውን ሴት በማግኘት ጥልቅ ዕውቀት ያላት መሆኑንም የተረዱበት አለ፡፡
ባትማር፤ ከቤት ባትወጣና ዕድሉን ባታገኝም ተፈጥሮ ሴቷን ለችግሮች መፍትሄ የሚሆን ሀሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ብዙ ዕውቀቶች ችሯታል ይላሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ ተነስተው እናትነትንና ሴትነትን የሚገልፁበት ቃላት ያጥራቸዋል፡፡ ‹‹ማህበሩን ልመሰርት የቻልኩት ከዚህ አስተሳሰብ ተነስቼ ነው፡፡ እኔ በራሴም ሆነ በልምድ እንዳየሁት ሴት ሁኔታዎች ከተመቻቹላት በእርግጥም ትሰራለች የሚል ዕምነት አለኝ›› ይላሉ ‹‹የሴቶች ይችላሉ›› መስራቿ ማህበሩን ለመመስረት ስላነሳሳቸው ሁኔታ ሲያብራሩ፡፡
ዳይሬክተሯ እንደሚናገሩት ከጠቅላላው የሕብረተሰብ ክፍል 51 በመቶ የሚሆኑትን ሴቶች ናቸው፡፡ ሆኖም የብዛታቸውን ያህል ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡ ተጠቃሚ ሊሆኑ ካልቻሉባቸው ምክንያት አንዱና ዋነኛው ሴቶች በሕብረተሰቡ ውስጥ የተዛባና ዝቅ የሚያደርጋቸው አስተሳሰብ ነው፡፡ ማህበሩ በተመሰረተ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቅድሚያ ከሰጣቸው ነገሮች መካከል ሴቶች ዕድሉን እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ይሄን ከሚያደርጉበት መንገድ አንዱ እችላለሁ የሚል አስተሳሰብ በውስጣቸው እንዲያዳብሩ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና ነው፡፡
ስልጠናው ኦሮሚያ፤ አማራ እና ደቡብ ክልልን ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉንም አካባቢዎች ተደራሽ የሚያደርግ ሲሆን በተለይ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ይተገበራል፡፡ ለአብነት ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተምረው ውጤታማ እንዲሆኑ ጥቃትን መከላከል የሚያስችል እና ሕይወት ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡
‹‹ወደ መከላከል የሚሄዱት በቅድሚያ ስለ ጥቃት አውቀው በመሆኑ በስልጠና ሊደርስባቸው ስለሚችለው ጾታዊ ጥቃት በሚገባ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እናደርጋለን›› የሚሉት ዳይሬክተሯ ስልጠናው አንዲት ሴት ካልተማረች የሚደርስባት ፈተና እና ውድቀት፤ ከተማረች ደግሞ የምትወጣበት ማማ ምን እንደሚመስል ታዳጊ ሴት ተማሪዎች ግንዛቤ እንዲያገኙ የሚደረግበት እንደሆነም ያነሳሉ፡፡
‹‹ያለ ወንዶች አጋርነት በየደረጃው ያለውን በስርዓተ ጾታ ረገድ የሚታይ የፍትሃዊነት ክፍተት ማመጣጠን አይቻልም›› የሚሉት ዳይሬክተሯ ወይዘሮ የምወድሽ ማህበሩ የነዚህ ሴት ተማሪዎች ወንድ አጋሮችም ስልጠናውን እንዲወስዱ የሚያደርግበት ሁኔታ መኖሩንም ይጠቁማሉ፡፡ ስልጠናው ታዳጊ ወጣት ወንድ አጋሮቹ ሴት ተማሪዎቹ ጓደኞቻቸውና ወንድሞቻቸው መሆናቸውን በተገቢው መንገድ እንዲገነዘቡ የሚያደርግ ነው፡፡
በመሆኑም ወንድ ተማሪዎች የወንድ አጋርነት ክበብ መስርተው ከሴት ተማሪዎች ጋር በጋራ በመንቀሳቀስ በሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርስን ጾታዊ ጥቃት እንዲከላከሉ የሚያስችል ውጤት ማምጣት ወንድ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በየትምህርት ቤቱ ያሉ መምህራን በቅንጅት በመሥራት እንዲከላከሉም ይሰራል፡፡ ስልጠናውንም እንዲወስዱ ያደርጋል፡፡
ሥራው እየተተገበረባቸው ካሉ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል በአዲስ አበባ የሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ አየር ጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከነዚህ ትምህርት ቤቶች ቀዳሚ መሆናቸውን ዳይሬክተሯ ያወሳሉ፡፡ ከፕላን ኢንተርናሽናል ጋር አራቱን ትምህርት ቤቶች ጨምሮ ለሁለት ዓመት በትምህርት ቤቶች በጉዳዩ ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት አቅደው ወደ ሥራ ገብተው የነበሩ መሆናቸውን ያስታውሳሉ፡፡
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻም 1ሺ400 ሴት ተማሪዎችንና 600 ወንድ ተማሪዎችን በማሰልጠን ስለ ስርዓተ ጾታ በቂ የሆነ ዕውቀት እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉንም ያነሳሉ፡፡በተለይ ሴት ተማሪዎች ባገኙት የአቅም ግንባታ ስልጠና ትኩረታቸውን ትምህርታቸው ላይ አድርገው ራሳቸውን ከጥቃት መጠበቅ በመቻላቸው ማህበሩ ጥሩ አፈፃፀም ማሳየት መቻሉ በሌሎች አካላት መረጋገጡንም ያነሳሉ፡፡
ሌሎቹ ማህበሩ ከዚሁ ከአቅም ግንባታ ጋር ተያይዞ እየሰራባቸው የሚገኙ ሥራዎች በርካታ ቢሆኑም በሴት አዳሪዎች ላይ የሚሰሩት የአቅም ግንባታና የድጋፍ ሥራ ሳይጠቀስ የሚያልፍ አይደለም፡፡ ‹‹አንዲት ሴት ወደ ሴት አዳሪነት የምትገባው ወድዳ ሳይሆን ሕይወቷን ለማቆየት ነው ብዬ አምናለሁ›› የሚሉት ዳይሬክተሯ ማህበሩ ከሥራዋ ጋር ተያይዞ በሚደርስባት ጾታዊ ጥቃትና በሚገጥሟት የተለያዩ የጤና ችግሮች ዙርያ እንደሚሰራም ያነሳሉ፡፡
ሥራውን ሼርኔት ከተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመቀናጀት በተለይ ልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ ባሉ ሴት አዳሪዎች ላይ የሚሰራ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡ በሥራው ከተሰማሩት አብዛኞቹ በቀጠሯቸው ባለ መጠጥ ቤቶች አማካኝነት ሳያስቡት የመጠጥ እና የሌሎች ደባል ሱሶች ተገዢ ሆነው በመቅረት ሕይወታቸው የሚበላሽበት አጋጣሚ መኖሩን ይናገራሉ፡፡
በሥራው በሚቆዩበት ጊዜ ከወሲብ ደንበኞቻቸው የሚደርስባቸውን ጥቃት እንዲሁም እርግዝና፤ ኤች አይቪና ሌሎች የአባላዘር በሽታዎችን መከላከል በሚችሉበት ዙርያ ስነተዋልዶና ሕይወት ክህሎት ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና በሥራው ለተሰማሩ ሴቶች እየተሰጠ የሚገኝበት ሁኔታ መኖሩንም ነግረውናል፡፡ ከሴት አዳሪነት ተላቅቀው በሌላ የገቢ ማስገኛ ሥራ እንዲሰማሩም ማህበሩ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ቡና ጠጡ በማህበሩ እየተተገበረ የሚገኝ ሌላው መርሐግብር ሲሆን ሴቶች ዘና እያሉና ከሌሎች ጋር በመገናኘት በማህበራዊ ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እርስ በእርስ በመወያየት ችግሮቻቸውን የሚፈታ ዕውቀት የሚገበዩበት እንደሆነ ያወሳሉ፡፡ በመርሐ ግብሩ በየመንደሩ በቤት ውስጥ የሚውሉ የቤት እመቤት ሴቶች፤ የቢሮ ሠራተኞች መምህራንና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
ማህበሩ ከአቅም ግንባታ ጋር ተያይዞ ሴቶች ከሕግና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር መብቶቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን በሚያስከብሩበት ሁኔታ ይሰራል፡፡ ዳይሬክተሯ የምወድሽ እንደሚናገሩት በዚህ ዙርያ እንደ አህጉረ አፍሪካ ከነሶማሌ፤ ሱዳን፤ ዑጋንዳ፤ ኬንያና ሌሎች አገራት ጋር በመቀናጀት ከሰሯቸው ሥራዎች መካከል የማፑቶው ስምምነት ላይ የሰሩት ይጠቀሳል፡፡
‹‹ሴቶችን አስመልክቶ የተፈረሙ ውሎች ሁሉ በራሳቸው በተጠቃሚ ሴቶቹ ጫና እስካልተደረገባቸው ድረስ ይተገበራሉ ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም መፈረማቸው በራሱ አንድ ነገር ነው›› የሚሉት ወይዘሮ የምወድሽ ለአብነት የማፑቶ ስምምነትን ያልፈረሙ የአፍሪካ አገሮች እንደነበሩም ለስልጠናው ከአገር ውጪ በሄዱባቸው ቦታዎች ለማየት መቻላቸውንም ያስታውሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው በርካታ ውሎች መካከል የማፑቶው ስምምነት ሌላው ማህበራቸው እንደ አገር ሲሰራበት ከቆየ ጉዳይ አንዱ መሆኑንም ገልፀው ከሥራው በፊት በውሉ ሴቶችን የሚመለከቱትን ያልፈረሙ አገሮች እንዲፈርሙ የሚያስችል ቅስቀሳ እንዲያደርጉ ስልጠና ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን ማህበሩ ይሄን ስልጠና መሰረት አድርጎ በአገሪቱ ወዳሉ ክልሎች አውርዶ ሰፊ ቅስቀሳ በማድረግ ስልጠና የሰጠበት ሁኔታ መኖሩንም ይጠቅሳሉ፡፡
እሳቸው ካንፓላን ጨምሮ እንደ አህጉርም ብቅ ብለው የማፑቶውን ስምምነት ያልፈረሙ አገራት የመኖራቸውን ልየታና የልምድ ልውጥውጥ ከአቻ ማህበራት ጋር ካደረጉ በኋላ ወደ አገር ቤት ተመልሰው ከኦሮሚያ ክልል፤ ከደቡብ ክልል፤ ከአማራ ክልል ጋር በመሆን ሰፊ ቅስቀሳ በማድረግ የአቅም ግንባታ ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸውንም ያወሳሉ፡፡ በዚህም ፊርማው ኢትዮጵያን ጨምሮ ባልፈረሙ አገሮች መፈረም መቻሉንም ይጠቅሳሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት የማህበሩ ዋና ሥራ የአቅም ግንባታ ቢሆንም ሴቶችን የሚጠቅሙና የሴቶችን ትልቅነት የሚያሳዩ ሥራዎች እየሰራ ያለም ነው፡፡ሴቶች ሥራቸውን ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ግፊት ያደርጋል፡፡ ‹‹ሴቶች ብዙ ሥራ እየሰሩ አደባባይ አይወጡም፡፡ ወንዱ ግን ትንሽ ሰርቶ አደባባይ በመውጣቱ ከነሱ በላይ የሰራ ይመስል እውቅና ያገኛል፡፡ በዚህ ላይ ማህበራዊ መስተጋብሩም በጓደኝነት አብሮ በመብላትና መጠጣት የተጠናከረ መሆኑ ያግዘዋል›› የሚሉት ዳይሬክተሯ ሴቶች ሳይፈሩና ዕድላቸውን በቸልታ ሳያሳልፉ አደባባይ መውጣት፤ ማስተማር፤ ራሳቸውን መግለጽ በሚችሉበት ሁኔታ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ ሴቶች ከሚዲያ ጋር መተዋወቅ፤ ራሳቸውን መግለጽና ሥራቸውን ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡ ማህበሩ ኤፍ ኤም 94 ነጥብ 3 ላይ ‹‹የምወድሽ ገጾች›› የሚልና በቅርቡ አምስት ዓመቱን ያከበረ ሳምንታዊ የቀጥታ ውይይት የሬዴዮ ፕሮግራም ሲኖረው በዚሁ እየታገዘ ሥራዎችን የሚያከናውንበት አግባብም አለ፡፡
በአምስት ዓመት ውስጥ ለኢትዮጵያ ትላልቅ ሥራ ሰርተው ያለፉና ለበርካታ ሴቶች አርአያ የሚሆኑ ባለውታ ሴቶች ታሪክ ምን እንደሚመስል እየተቀነጨበ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ የተለዩ ሴቶችና ሴት አዳሪዎች ስለራሳቸው ከመግለጽ ባሻገር ድምፃቸውንም እያሰሙበት ይገኛሉ፡፡ በየቤቱ ያሉ ሴቶችን እየጋበዘ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በሕይወታቸው ላይ የሚያሳድረው ጫና፤ ሕጉ የሚለው፤ አፈፃፀሙ ላይ ያለው ችግር ውይይት ይደረግበታል፡፡ ስለ ሴቶች ጤና፤ ፖለቲካዊ ተሳትፎ፤ ውሳኔ ሰጪነት፤ እኩልነትም ይወራበታል ብለውናል፡፡
ማህበሩ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሴት ተማሪዎች ፆታዊ ጥቃትን እንዲከላከሉና ከወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ (ፓድ) ጀምሮ የሚያስፈልጋቸውን የሚያሟላቸው ከፕላን ኢንተርናሽናል በሚያገኘው ድጋፍ ሲሆን በሴት አዳሪዎች ዙሪያ ለሚሰራው ደግሞ በሼር ኔት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚደረግለት የገንዘብ ድጋፍ እንደሆነ ነግረውናል፡፡
ቤተልሄም ታደሰ የአየር ጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪና የትምህርት ቤቱ የስርዓተ ጾታ ክበብ ተጠሪ ስትሆን ሴት ተማሪዎች ከወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ጀምሮ ምን ዓይነት ችግሮች እንዳሉባቸው በማግባባት ትጠይቃለች፡፡“ብዙ ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸው ለነሱ ፓድ የመግዛት አቅም ስለሌለው የወር አበባ በሚሆኑበት ጊዜ እንደሚቀሩ ነግረውኛል” የምትለው ቤተልሔም ዘንድሮ “ሴቶች ይችላሉ”የተሰኘው ማህበር ባደረገላቸው የፓድና የውስጥ ሱሪ ድጋፍ ችግሩን መቅረፍ መቻላቸውን ትገልፃለች፡፡
ትምህርት ቤት በሚዘጋበት ጊዜ እንዳይቸገሩ ከሰኔ እስከ ነሐሴ የሚጠቀሙበት ፓድና የውስጥ ሱሪ እንደሚታደል ነግራናለች፡፡ ተማሪዋ ማህበሩ ሴት ተማሪዎች ስለ ስርዓተ ጾታና ጾታዊ ጥቃት በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ጥቃቱን እንዲከላከሉ ለእሷና ለሌሎች የወንድ አጋር ተማሪዎች ስልጠና መስጠቱንም ነግራናለች፡፡ እነሱ በፊናቸው አጭር መልክት ባለው ድራማና ጭውውት የመደፈር ጥቃት የደረሰባት ሴት ከመደፈሯ በፊትና በኋላ የሚኖራትን ሁኔታ በማስተላለፍ ሴትና ወንድ አጋሮች በውስጣቸው እንዲያሰርፁ እያደረጉ ነው፡፡
‹‹በትምህርት ጊዜ መቀለድ በራስ ላይ መቆመር ነው። አንደንዶች ባለማወቅ ዕድሜያቸውን ያሳጥራሉ፡፡ በጓደኛ ግፊት በአልባሌ ነገሮች ተሸንፈው የሱስ እስረኛ ሆነው ይቀራሉ እኔም 9ኛ ክፍል ላይ በጣም ተሳስቼ ሲጋራ ሞክሬ ነበር፤ ዕድሜ ለእናቴ አልቅሳ መክራኝ አባብላ መለሰችኝ። ዛሬ ጎበዝ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ ነገ ደግሞ ለአገሬ የምሠራ ልሆን እችላለሁ የሚል ተስፋ ይዤ እየተማርኩ ነው ያለን ደግሞ የወንድ አጋርነት ማህበር አባል ሆኖ በሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊና ማንኛውንም ጥቃት እየተከላከለ የሚገኘው ተማሪ ኤሊያስ ተሻለ ነው፡፡
ተማሪ ኤሊያስ “በአንተ ላይ ሊያደረጉብህ የማትፈልገውን በሌሎች ላይ አታድርግ” የሚለውን ቃል መሰረት አድርጎ አየተንቀሰቀሰ እንደሆነም ይናገራል፡፡ የወንዶች አጋርነት ቡድን አባል ሆኖም በሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርስ ጥቃትን አጥብቆ እንደሚቃወም ነግሮናል፡፡ ዕድሜዋ ወደ 22 የሚጠጋውና በሴት አዳሪነት ሥራ የምትተዳደረው ሜሮን ሰይፉ በ13 ዓመቷ ከገጠር ወላጆቿ ቤት አስተምራታለሁ ብላ አምጥታት በሥራው እንድትሰማራ ያደረገቻት አንዲት ዘመዷ እንደሆነች ትናገራለች፡፡
‹‹ሴቲቱ አላስተማረችኝም፤ አነስተኛ ቡና ቤት ስለነበራት ኮማሪት ነው ያደረገችኝ›› ስትል ታስታውሳለች፡፡ ይሄም ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም የአልኮል መጠጥ ልጋብዝሽ ላላት ወንድ ሁሉ እንቢ ማለትና ገበያዋን መዝጋት እንደሌለባት በየጊዜው ስለምታሳስባት ከወንዶች ጋር ከማደር በተጨማሪ የመጠጥ ሱሰኛ ለመሆን እንደተገደደችም ትናገራለች፡፡
‹‹አሁን ላይ ከወንዶች ጋር አንሶላ ተጋፍፌ የማገኘውን ገቢ ለምግብና ለቤት ኪራይና የመጠጥ ሱሴን ለማርካት አውለዋለሁ ›› የምትለው ሜሮን ‹‹ሴቶች ይችላሉ›› ማህበር እሷንና የመሰል ሱስ ተገዢ የሆኑትንና በልደታ ክፍለ ከተማ በሴት አዳሪነት የተሰማሩትን ሴቶች ሰብስቦ የአቅም ግንባታና ራሳቸውን ከኤች አይቪና ከሌሎች በሽታዎች የሚከላከሉበት የስነ ተዋልዶ ስልጠናና የስነ ልቦና ትምህርት በመስጠት ከሱስ ተገዢነት ለማላቀቅ እየሰራ መገኘቱን ታነሳለች፡፡
በዚህም የመነሻ ገንዘብ ቢያገኙ ሥራቸው መለወጥ የወደፊት ዕቅዳቸው መሆኑን ትጠቁማለች፡፡ በቅርቡ እሷን ጨምሮ ለ20 ሴቶች መነሻ ድጋፍ አድርጎላቸው የራሳቸውን የገቢ ማስገኛ ሥራ እንዲሰሩ ሁኔታዎችን እያመቻቸላቸው መሆኑንም ትናገራለች፡፡ የምወድሽ ገጽ በሚለው የኤፍ ኤም ሬድዮ ፕሮግራም ከነሱ ታሪክ ሌሎች እንዲማሩ የሚያደርጉበት ዕድል እንደሰጣቸውና በተለይ በኮቪድ ጊዜ በፕሮግራሙ ስም ድጋፍ ሲያደርግላቸው መቆየቱን ነግራናለች፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2015