አዲስ አበባ፡- ለፕሬስ ነጻነት የምናደርገው ትግል ለጋዜጠኞች መብት ስንል የምናደርገው ሳይሆን ለራሳችን መብት ስንል የምናደርገው ትግል ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ።
ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ቀንን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ትናንት ይፋ ባደረጉት የጽሑፍ መግለጫ ‹‹የፕሬስ ነጻነትም የራሳችን ነጻነት ነው። የሠለጠነና የዘመነ ማኅበረሰብ እንዲኖረን የሠለጠነና የዘመነ ፕሬስ ያስፈልገናል።
የሠለጠነና የዘመነ ፕሬስ ስንልም መብቱን የሚያስከብር፣ ኃላፊነቱንም የሚወጣ ነው። መብት የሌለው ኃላፊነት ባርነት ነው፤ ኃላፊነት የሌለው መብትም ልቅነት ነው። እኛ ደግሞ ባርነትንም ሆነ ልቅነትን አንፈልጋቸውም›› ብለዋል።
ባለፉት ወራት በዋጋ ጭማሪ ምክንያት የጋዜጣ ወረቀት ከ70 በመቶ በላይ ጨምሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ግን ይሄ ጭማሪ በጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ እንዲጨመር አልፈቀደም። በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በኩል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ጭማሪ ራሱ መንግሥት ድጎማ አድርጎ ተሸክሞታል። ይህንን ያደረግነው የፕሬስ መብት የኛም መብት ስለሆነ ነው ብለዋል።
ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ቅድሚያ በመስጠት ባለፈው አንድ ዓመት አያሌ የለውጥ ርምጃዎችን መወሰዳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስተው ፣እድሜ ልክና ሞት የተፈረደባቸው የመንግሥት ተቃዋሚዎች ከእሥር መፈታታቸውን፤ ተዘግተው የነበሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንደገና ወደ ህትመት ብርሃን መምጣታቸውን፤ ከሀገር ውጭ ሆነው የኖሩ ሚዲያዎች በነጻነት ወደ ሀገር ቤት መግባታቸውንና ከ260 በላይ ተዘግተው የነበሩ ብሎጎችና ድረ ገጾች መከፈታቸውን ዶክተር አቢይ አብራርተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ መንግሥት የፕሬስ ነጻነት መብት በሚገባ እንዲከበር ብዙ ሥራዎች ቢሠራም ሌሎች ብዙ ሥራዎች ደግሞ ይቀሩታል። የሚዲያዎችን አቅም ለማሳደግ፣ የሥልጠናና የልምድ ልውውጥ ዕድሎችን ለማመቻቸት፣ ለሚዲያ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን የቀረጥ ዋጋ ለመቀነስና መረጃ ለማግኘት ያለውን ፈተና ለመቀነስ ይሰራል።
‹‹በሽግግር ውስጥ ያለ ማኅበረሰብን ለማገዝና ለማሻገር የሚያስችል የሚዲያ ከባቢያዊ ሁኔታ ያስፈልገናል››ያሉት ዶክተር አቢይ ፣ ከግጭት ቀስቃሽነት፣ ከጠብ ጫሪነት፣ ከአሉባልታ አነፍናፊነትና ከስሜታዊነት የራቀ ፕሬስ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።በተለይም በቀጣዩ ዓመት ከሚካሄደው ምርጫ ጋር ተያይዞ በእውነት፣ በዕውቀትና በሚዛናዊነት የሚሠራ ፕሬስ ሊኖር ይገባል ብለዋል።
በፕሬስ ነጻነትና ዕድገት ላይ የሚሠሩ አካባቢያዊ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ፕሬስ ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል ።
በተመሳሳይ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት የሰጣቸውን የሰላም ሽልማት አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ በሸራተን አዲስ ባደረጉት ንግግር፣ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች በኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የታሰረ ጋዜጠኛ እንደሌለ መስክሯል፤ ይህ በሆነበት ዓለም አቀፉን የፕሬስ ነጻነት ቀን ስናከብር ትልቅ ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት የፖሊሲ ማሻሻያዎችን አድርጓል። ዴሞክራሲያዊ አሰራር ተዘርግቷል፤ ይህም በመገናኛ ብዙኃን ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ያለፈው አንድ ዓመት ለውጥ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነትን አጎናጽፏል። የዕድሜ ልክ እስራትና የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሁሉ ተለቀዋል። ከአሥር በላይ ተሰደው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገራቸው ገብተው ሰላማዊ ትግል እያደረጉ ነው። ይህም ከአፈሙዝ ይልቅ በሃሳብ መታገልን ያሳየ ነው ።
ነፃነት በኃላፊነት መሆን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መገናኛ ብዙኃንም ሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች መረጃን ሲጠቀሙ ስነምግባሩን የተከተለ መሆን አለበት። የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ማግኘት ማለት የጥላቻ ንግግርና የሀሰት ዜና ለማሰራጨት መሆን የለበትም። ከስሜታዊነት ወጥቶ ትክክለኛ ዘገባ መሰራት አለበት። መገናኛ ብዙኃን ማህበረሰቡን የሚገነባና የሚቀርጽ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
በጋዜጣው ሪፖርተሮች