አዲስ አበባ፡- ያለህግ አስገዳጅነት በፈቃደኝነት የመክፈል ባህል በ32 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የአፍሪካ ልማት ባንክ ጥናት አመላከተ። በጥናቱ የተገኙ ምክር ሃሳቦች በፖሊሲ ማዕቀፍ ተካተው እንዲተገበሩ የሚደረግ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ።
በአፍሪካ ልማት ባንክ የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ አበበ ሽመልስ ትናንት ጥናቱ በሸራተን ሆቴል ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደገለፁት፤ በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡ ያለአንዳች አስገዳጅነት ግብር የመክፈል ባህሉ ከ12 በመቶ በታች የነበረ ሲሆን ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ግን በተከናወነው ህብረተሰብ አቀፍ የንቅናቄ ሥራ 32 በመቶ መድረስ ችሏል።በዚህም የገቢዎች ሚኒስቴር ወደ 750 ሺ ዶላር ገቢ አግኝቷል።
ይሁንና አገሪቱ ካላት እምቅ ሃብት አንፃር እየገባ ያለው ገቢ አሁንም ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን በጥናቱ መረጋገጡን ያስረዱት አቶ አበበ፤ ባንኩ ባደረገው ጥናት ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ካገኘ በገዛ ፍቃዱ ታክስና ግብሩን ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ጥናቱ የዳሰሳቸው ናሙናዎች እንደሚያስረዱም ተናግረዋል። ለገቢው አነስተኛ መሆን ደግሞ በዋናነት ገቢ ሰብሳቢው ተቋም እስካሁን የሰበሰበውን ገቢ የትና በምን ሥራ ላይ እያዋለ ስለመሆኑ ለህዝቡ ግልፅ ያለማድረጉ ጥርጣሬ መፍጠሩን አስረድተዋል።
በመሆኑም መንግሥት ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ ስለመሆኑ እያስጨበጠ ካለው ግንዛቤ ጎን ለጎን የተሰበሰበው ገቢ በተጨባጭ ሥራ ላይ እየዋለ ስለመሆኑ ማሳያዎች ለህዝብ ማቅረብ እንደሚገባ በጥናቱ ከተቀመጡ ምክረ ሃሳቦች መካከል ዋነኛው መሆኑን አስረድተዋል። በተጨማሪም ፍትሃዊ የግብር አከፋፈል ስርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባና ከብልሹ አሰራር ዘርፉን ማላቀቅ እንደሚጠበቅበትም ጥናቱ መጠቆሙን አመልክተዋል።
በሌላ በኩልም አሰራሩን የማዘመንና በቴክኖሎጂ የመደገፉ ጉዳይ አሁንም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ አበበ ገልፀው፣ ለዚህ ደግሞ ባንኩ የገቢዎች ሚኒስቴርን አቅም ለመደገፍ የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርፆ እየሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፤ ባንኩ ያደረገው ጥናት መንግሥት በቅርቡ የውስጥ ገቢ ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት የሚያግዝ በመሆኑ የተሰጡ ምክረሃሳቦች በፖሊስ ማዕቀፍ ማሻሻያ ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ ሥራ ላይ እንዲውሉ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል። በተለይም ከግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ጋር ያለው ግንኙነት በመግባባት ላይ የተመሰረተ ሁሉም ለአገራዊ እድገት በፈቃዱ የበኩሉን ድርሻ መወጣት የሚያስችሉ አሰራሮችን በፖሊስና በህግ ማዕቀፍ እንዲካተቱ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
«ጥናቱ የመንግሥት የፋይናንስ የልማት አቅርቦትን ለማሻሻል በአገር ውስጥ ገቢን የመሰብሰብ አቅማችን ማሳደግ ወሳኝ መሆን ያመላክታል» ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግሥት ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ገቢ ሰብሳቢ ተቋሙን በሚኒስቴር ደረጃ ከማቋቋም ባለፈ በሚኒስትሩ የሚመራ ግብረኃይል በማቋቋም ተቋማት ለገቢው ማደግ ተቀናጅተው እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል። በየተቋሙ እየተደረጉ ያሉ ሪፎርሞችን የውስጥ ገቢን የማሳደግ አቅምን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ በሚያስችሉ መልኩ እንዲቃኙ ይደረጋል ብለዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ደግሞ ጥናቱ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ግብር የመክፈል ባህል አሁንም ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን የሚያመላክት ከመሆኑም ባሻገር ህግን ለማስከበር የሚደረገው ጥረትም ውጤት እያመጣ መሆኑንም ለመገንዘብ ያስቻለ መሆኑን አመልክተዋል። «ይሁንና ህግን ለማስከበር ባልሄድንባቸው ጊዜያት ክፍያዎች እንደማይፈፀሙም በተጨባጭ ጥናቱ አሳይቷል» ብለዋል።
በመሆኑም ከጥናቱ በተሰጠው ምክረ ሃሳብ በመነሳት በአንድ በኩል ህግን የማስከበር ጥረቱ ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን መንገድ በሌላ በኩልም ህብረተሰቡ የገቢ አሰባሰቡ መሪ ተዋናይ የሚሆንበትን አካሄድ መቀየስ ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ጥናት እንደሚያ መለክተው፤ በአዲስ አበባ ብቻ በአግባቡ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ገቢ ቢሰበሰብ በዓመት 25 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የሚቻልበት ዕድል አለ። ይህም የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠልና ለበርካቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከፍተኛ አቅም ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
ማህሌት አብዱል