– የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ
አዲስ አበባ፡- ጃፓን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በአገር ውስጥ የሚሰሩትና በውጭ ሀገር በዲፕሎማሲው ረገድ የሚያደርጉትን ጥረት እንደምታደንቅ ተገለፀ። የጃፓን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ታሮ ኮኖ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጠቅሶ የጃፓን ኤምባሲ ለዝግጅት ክፍላችን በአደረሰን መረጃ እንዳመለከተው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለአካባቢው ሰላም እየወሰዱት ያለውን የመሪነት ሚና ጃፓን ከፍተኛ አድናቆት ትሰጠዋለች ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያና በዙሪያዋ ባሉ አገራት በርካታ ታሪካዊ ዳራ ያላቸው ለውጦች መታየታቸውን ሚስተር ኮኖ ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የአፍሪካ ቀንድን ወደ ሰላም የማምጣት ጥረትን እንደ መሩ አመልክተዋል። ከኤርትራ ጋር የድንበር ግጭትን በማስወገድና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን እንደገና ማስጀመራቸው ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
ጃፓን ለአፍሪካ ቀንድና አካባቢው ሰላም መረጋጋት በተባበሩት መንግሥታት ስር የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ እንደቆየች ያስታወሱት ሚስተር ኮኖ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን እንደገና መጀመራቸውን ተከትሎ ጃፓን አፍሪካውያን የራሳቸውን ግጭቶች በራሳቸው የሚፈቱበት ጊዜ አሁን ነው ብላ እንድታምን ማድረጉን ገልፀዋል።
የፊታችን ነሐሴ ጃፓን 7ኛውን የቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ልማት ኮንፍረንስ (ቲካድ7) ታዘጋጃለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ጉብኝትም የአፍሪካ አገሮች ለቲካድ7 ስብሰባ ስኬት ትብብር እንዲያደርጉ ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ስብሰባ አፍሪካውያን በራሳቸው ተነሳሽነት እያራመዱት ያለው የሰላም ጥረት ዋና ሃሳብ ሆኖ እንደሚነሳ ጠቁመው፣ ጃፓንም በአፍሪካ የሰላም ግንባታ ጥረት አገራዊ ተቋማትን በመገንባት ረገድ እገዛዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ቃል ገብተዋል።
ሚስተር ኮኖ በአሁኑ ጉብኝታቸውም ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተላከ የቲካድ7 ስብሰባ የተሳትፎ ጥሪ ደብዳቤ እንደሚያቀርቡ ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ስለ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት በሚደረገው ውይይት ከጃፓን ጋር በመሆን እንዲመሩ መጋበዛቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
በቦጋለ አበበ