አቶ አብርሃም ደስታ ነዋሪነታቸው በጋምቤላ ከተማ ነው። በሙያቸው ደግሞ ፋርማሲስት ናቸው። ይህንኑ ሙያቸውን ተጠቅመው መድሃኒት ጋምቤላ ላይ ይሸጣሉ። በዚሁ የመድሃኒት ንግድም ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ። በሕይወታቸውም ደስተኛ ናቸው። አንድ ነገር ግን ሁሌም ያሳስባቸዋል። እርሱም ሆሳዕና የሚኖሩት የታላቅ ወንድማቸው ጉዳይ ነው።
አንድ ቀን ታላቅ ወንድማቸው አቶ አለማየሁ ደስታ፣ በድንገት አሟቸው ይወድቃሉ። ይህንን የሰሙት አቶ አብርሃም፣ በፍጥነት ወንድማቸው ወደሚኖሩበት ሆሳዕና ከተማ ያቀናሉ። እዛ ደርሰው ወንድማቸውን ወደ አንድ የህክምና ጣቢያ ይወስዳሉ። የጭንቅላት ህመም ሊሆን እንደሚችል የገመቱት የህክምና ባለሙያዎቹ የኤም.አር.አይ ምርመራ ያዛሉ።
ነገር ግን የምርመራ ውጤቱ አቶ አለማየሁ የገጠማቸው የጭንቅላት ህመም ምን እንደሆነ በትክክል ስለማያሳይ አዲስ አበባ ሄደው እንዲታዩ ትእዛዝ ያስተላልፋሉ። አቶ አብርሃምም ትእዛዙን ተቀብለው ወንድማቸውን ወደ አዲስ አበባ ይዘው ይመጣሉ። ቦሌ አካባቢ ወደሚገኝ አንድ የግል ጤና ተቋም ወስደው ሲያስመረምሩ ወንድማቸው በጭንቅላታቸው ውስጥ እጢ እንዳለባቸው ያረጋግጣሉ።
በወቅቱ አቶ አብርሃምን ያሳሰባቸው ወንድማቸው ያጋጠማቸው የጭንቅላት ህመም ብቻ ሳይሆን ህመሙ በቀዶ ህክምና የሚስተካከል ቢሆንም ከቀዶ ህክምናው በኋላ የሚሰጠው ተጨማሪ የጨረር ህክምና በኢትዮጵያ አለመኖሩ ነበር። የህክምና ባለሙያዎቹም ብቸኛ ምክር ህክምናው በሀገር ውስጥ ስለሌለ ወንድማቸውን ወደ ውጭ ሀገር ወስደው እንዲያሳክሙ ነበር።
በእርግጥ አቶ አብርሃም በጊዜው ወንድማቸውን ወደ ውጭ ሀገር ልከው የማሳከም አቅም ነበራቸው። አጠቃላይ የህክምና ሂደቱን ጨርሶ ወንድማቸውን አሳክሞ የሚመልስ አካል ግን ማግኘት አልቻሉም። በዚህ ጭንቅ ሰአት ነበር አንድ ስልክ እጃቸው ውስጥ የገባው። ወዲያው ደወሉ።
ሙሉ ሂደታቸውን በመጨረስ ወንድማቸውን በህንድ፣ ቻይና አልያም ቱርክ ሀገር በመውሰድ ሊያሳክሟቸው እንደሚችሉ ከነሙሉ ማብራሪያውና የህክምና ዋጋ ጭምር ነገሯቸው። እርሳቸውም ይሻለኛል ያሉትን መርጠው ወንድማቸውን በህንድ ሀገር ለማሳከም ወሰኑ።
አስፈላጊውን የህክምና ወጪ በመፈፀምና የህክምና ታሪክ መረጃዎችን በማቅረብ ወንድማቸውን ይዘው ወደ ህንድ ሄዱ። ወንድማቸውም የተሟላ ህክምና በህንድ ሀገር ለአንድ ወር ተከታትለው ከሁለት ወር በፊት በተሟላ ጤና ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
ይህ አቶ አለማየሁ የተሻለ ህክምና በውጭ ሀገር አግኝተው ጤናቸው እንዲመለስ እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለገለውና ለብዙ ወጣቶችም የስራ ፈጠራ ምሳሌ ሊሆን የቻለው ‹‹ጌት ዌል›› የተሰኘው የህክምና ጉዞ አማካሪ ድርጅት ነው።
ወጣት በጋሻው ባይለየኝ የህክምና ባለሙያና የጌት ዌል የህክምና ጉዞ ማማከር አገልግሎት ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ነው። ነፃ የትምህርት እድል አግኝቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በውጭ ሀገር ተከታትሏል። ወደሀገር ቤት ተመልሶም በጅማ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ተምሯል። የህክምና ትምህርቱን ካጠናቀቀ ለተወሰኑ ጊዜያት በሙያው ሰርቷል። በውጭ ሀገር የመስራት እድል ገጥሞት ለአስር ዓመታት በሙያው አገልግሏል።
ሀኪም ሲኮን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰዎች እየደወሉ የህክምና ምክር መጠየቃቸው አይቀርምና በጋሻውም ከቤተሰብ፣ ጓደኛና ጎረቤት የህክምና ምክሮች ይቀርቡለት ነበር። ሌሎች ሰዎችም በቀጥታ ወደእርሱ እየመጡ ህክምና ማግኘት እንደሚፈልጉም ተመልክቷል። ይህንኑ በማየትና የህክምና ሙያውን ዘርፍ ወደ ቢዝነስ መቀየር እንዳለበት በመረዳት የሁለተኛ ዲግሪውን በቢዝነስ አስተዳደር ለንደን ከሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ተከታትሎ ጨረሰ።
የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱ መመረቂያ ፅሁፍ ያተኮረውም በኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገር ተጉዞ ህክምና ከማግኘት ችግር ጋር የተያያዘ ነበር። ጥናቱም በዚህ ህክምና ኢትዮጵያ ምን ያህል እንዳደገች፣ ምን ያህል ኢትዮጵያውያንስ ህክምና ፈልገው ወደ ውጭ ሀገር እንደሚሄዱና ችግሩስ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ዳሷል። የዚህን ጥናት ውጤትም ነው ወጣት በጋሻው ወደ ስራ ፈጠራ የቀየረው።
በዚሁ ጊዜ ወጣት በጋሻው ሀኪም ሆኖ የገጠመው የቤተሰብ ችግርም በሀገር ውስጥ የሌለውን ህክምና በውጭ ሀገር አፈላልጎ እንዴት ማሳከም እንዳለበት ፍንጭ ሰጥቶታል። በተለይ እናቱ ታመው በሀገር ውስጥ ህክምና ባለማግኘታቸው በውጭ ሀገር ለማሳከም ከፍተኛ ውጣ ውረድ አይቷል። እገረ መንገዱንም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ህክምና ለማግኘት የሚያጋጥማቸውን ችግር ተመልክቷል።
በዚህም ሰዎች ከኢትዮጵያ ውጭ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ከቪዛ ጀምሮ እስከ የጉዞ ቲኬት፣ ማረፊያ፣ ሆስፒታልና መግባቢያ ቋንቋ ከፍተኛ ችግር እንደሆኑም ተረድቷል። ህክምና ደግሞ ጊዜ የሚሰጥ ጉዳይ እንዳልሆነ፤ ታካሚውም ያለውን ገንዘብ አሟጦ ወደ ውጭ ሀገር የሚሄድ ከመሆኑ አኳያና በዚህ ሂደት ውስጥ የነበሩት ችግሮች የባለሙያ እርዳታ ቢያገኙ ይስተካከላሉ የሚል ፅኑ እምነትም ነበረው።
ህክምናን እኩል ማድረግ አይቻልም። ሀገራትም የሚገኙት በተለያዩ የህክምና ደረጃ ላይ ነው። በዓመት ከአሜሪካን ወደሌላው ሀገር የሚታከሙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንደሚጠጋም ከዓመታት በፊት የወጡ ጥናቶች ያሳያሉ። ባደጉት ሀገራትም የህክምና አሰጣጥ ልዩነቶች በየቦታው ይታያሉ። ኢትዮጵያን በመሰሉ ታዳጊ ሀገራት ደግሞ የህክምና እድገት ቢኖርም አሁንም ካለው የሳይንስ እምርታ ጋር ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ። ሕይወትን ሊታደጉ የሚችሉ የህክምና ሳይንሶች፣ እውቀቶችና ቴክኖሎጂዎች ቢኖሩም እነዚህን ባለማግኘት አሁንም በርካታ ታካሚዎች ሲሰቃዩ ይታያሉ። ከነዚህ ችግሮች በመነሳትም ነው ወጣት በጋሻው ጌት ዌል ሜዲካል ትራቭልን ያቋቋመው።
እርሱ እንደሚለው፤ ጌት ዌል ሜዲካል ትራቭል ስራውን የጀመረው መጀመሪያ አካባቢ አምስት ሰዎችን ይዞ በአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ነበር። ድርጅቱ ስራውን እንደጀመረ በተለያዩ ሀገራት ያሉ ሆስፒታሎችንና የሚሰጡትን የህክምና አገልግሎትና ለአገልግሎት የሚጠይቁትን ዋጋ ጠንቅቆ ለማወቅ ሞክሯል። የህክምና ተጓዦች ፍላጎት ምን እንደሆነም ለይቷል።
ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ የተሰራውን ጥናት መነሻ በማድረግ ቶሎ ወደ ስራ መግባት ተችሏል። ከዚህ ጊዜ አንስቶም ድርጅቱ በርካታ ሆስፒታሎችን ማቅረብና ብዙ ታካሚዎችን መርዳት ችሏል። አሁን ላይ በዚህ ዘርፍ ከተካኑ ድርጅቶች ውስጥም አንዱ ለመሆን በቅቷል።
ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአገልግሎታቸው ጥራት፣ ባላቸው የህክምና ባለሙያዎችና ቴክኖሎጂ ተቀባይነት ካላቸው ሆስፒታሎች ጋር ጥብቅ ትስስር ፈጥሮ ታካሚዎች መሄድ ይገባቸዋል ወይስ አይገባቸውም ከሚለው ጀምሮ ደርሰው ወደሀገራቸው እስኪመለሱ ድረስ ያለውን ሙሉ የህክምና ጉዞ አስተካክሎ በተመጣጣኝ ዋጋና በአጭር ጊዜ ህክምናውን አጠናቀው እንዲመለሱ ያደርጋል። ይህም የታካሚውን ጊዜና ወጪ ይቆጥባል ፤ እንግልትንም ይቀንሳል። ሀኪም ለሀኪም በሚያደርገው ንግግር የታካሚዎች ህክምና ታሪክ ተቀናብሮ እንዲደርስም ያስችላል።
በአሁኑ ጊዜም ድርጅቱ በአዲስ አበባ ሁለት ቢሮዎች ያሉት ሲሆን፣ በህንድ፣ ቱርክ፣ ታይላንድ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ አሜሪካንና ሀንጋሪ ሀገር ከሚገኙ አምስት ሆስፒታሎች ጋር በጥምረት ይሰራል። የሀገር ውስጥ ሆስፒታሎችም ታማሚዎቻቸው በሀገር ውስጥ ህክምና ማግኘት እንደማይችሉ ሲያረጋግጡ ከድርጅቱ ጋር በቅርበት ይሰራሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ‹‹በሀገር ውስጥ ህክምናቸውን እየተከታተሉ ያሉ ማናቸውም ታካሚዎች ወደ ውጭ ሀገር እንዲሄዱ ድርጅቱ አይመክርም›› የሚለው ወጣት በጋሻው፤ የድርጅቱ ዋነኛ ዓላማ ዜጎች በኢትዮጵያውያን ሀኪሞች ታክመው በሀገር ውስጥ ካለው ህክምና አቅም በላይ ሲሆን ለታካሚዎች እርዳታ መስጠት መሆኑን ይናገራል።
በዚሁ ዓላማ መሰረት ታካሚዎች በሀገር ውስጥ ያደረጉት ህክምና በቂ እንዳልሆነና ወደ ውጭ ሀገር ሄደው መታከም እንዳለባቸው በህክምና ባለሙያዎች ሲነገራቸው ወደ ድርጅቱ ይመጣሉ። የህክምና መረጃቸውን ይዘው ከመጡ በኋላም ከድርጅቱ የህክምና ባለሙያዎች ጋር ምክክር ያደርጋሉ። አንዳንዴም ተጨማሪ ምርመራ ካስፈለጋቸው በሀገር ውስጥ ካሉ ሆስፒታሎች ጋር በመሆን ምርመራ ይደረግላቸዋል። በዚሁ መሰረት ድርጅቱ በቂ ግንዛቤና መረጃ ይዞ የታካሚዎችን ፍላጎት፣ ጤና ሁኔታ፣ የመክፈል አቅምና የሆስፒታል ምርጫ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከተመረጡ የውጭ ሀገር ሆስፒታሎችና የህክምና ባለሙያዎች ጋር ባላቸው የህክምና ሪፖርት መሰረት ንግግር ያደርጋል።
በመቀጠል ታካሚዎች የሚያስፈልጋቸውን የህክምና ወጪ፣ የሚያስፈልጋቸውን ጊዜና ህክምናው ሊያመጣው የሚችለውን ለውጥ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ታካሚዎች ሲወስኑ ህክምናቸውን የማሰናዳት ስራ ይሰራል። ይህም የማሰናዳት ሂደት ቪዛቸውን ማግኘት፣ ኢንሹራንሳቸውን ማሰራት፣ የጉዞ ትኬታቸውን ማዘጋጀትና በዛ ሀገር የሚቀበሏቸውንና ቋንቋ የሚያስተረጉሙላቸውን ሰዎችና የሚያርፉበትን ቦታ ማስተካከልን ያካትታል።
በዚህ ህክምና ሂደት በሀገር ውስጥ ያሉ የታካሚ ቤተሰቦች ጭንቀት ውስጥ ስለሚገቡ ተከታታይነት ያለው መረጃ እንዲያገኙ ይደረጋል። የድርጅቱ ኬዝ ማናጀሮችም ከታካሚዎቹና ከሀኪሞቹ ጋር በጥምረት ንግግር እያደረጉ ታካሚው የተሻለና የተሳካ ህክምና እንዲያገኝ ያደርጋሉ። ታካሚዎች ህክምናቸውን አጠናቀው ወደሀገራቸው ከተመለሱም በኋላ ድርጅቱ ካከማቸው ሀኪም ጋር የሚገናኙበትን ድልድይ በመመስረት ቀጣይነት ያለው ህክምና እንዲኖራቸውም ያደርጋል።
ለዚህ አገልግሎትም ታካሚዎች የሚከፍሉት ክፍያ እንደህክምናቸው አይነትና እንደመረጡት የሆስፒታል አይነት ይለያያል። ነገር ግን ድርጅቱ ታካሚዎችን ተቀብሎ ለሚሰጠው ምክር አገልግሎት 400 ብር ያስከፍላል።
‹‹የስራ ፈጠራዎች መነሻ ችግር ነው›› የሚለው ወጣት በጋሻው አብዛኛዎቹ የስራ ፈጠራዎች ችግር ፈቺ መሆን እንዳለባቸውና ወጣቶችም በነዚሁ ችግር ፈቺ ስራ ፈጠራዎች ላይ አተኩረው መስራት እንዳለባቸው ይናገራል። እርሱም ካጋጠመው ችግር በመነሳት የህክምና ሙያውን ተጠቅሞ ወደዚህ ቢዝነስ እንደገባም ይጠቅሳል።
በተለይ ደግሞ በህክምናው ዘርፍ ተመርቀው ያለስራ የተቀመጡ በርካታ ወጣቶች እንደመኖራቸው መጠን በህክምና ጉዞ ማማከር አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የህክምናው ዘርፍ አማራጮች ውስጥ በመግባት ለአብነትም በቤት ለቤት ህክምና፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማማከርና የህክምና አገልግሎት የራሳቸውን ቢዝነስ በመፍጠር ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ይጠቁማል። ለዚህም በሚመለከተው አካል ተገቢ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያመላክታል።
የእርሱ ድርጅትም ታካሚዎች በውጭ ሀገር ለመታከም ሲፈልጉ የጉዞ ምክር አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ ስራ አጥነትን ለመቅረፍ ከውጭ ሀገር ሆስፒታሎች ጋር በመነጋገር አዳዲስ ወጣት ተመራቂ የህክምና ባለሙያዎች ተጨማሪ የህክምና ትምህርት ተምረው ወደሀገራቸው የሚመለሱበትን መርሃግብር በመቅረፅ ላይ እንደሚገኝም ያስረዳል። ለዚህም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ይጠቅሳል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ 25 ወጣት ሀኪሞችን በጥምረት ወደሚሰራባቸው ሆስፒታሎች በመላክ አጫጭር የህክምና ሥልጠናዎችን ወስደው ወደሀገራቸው እንዲመጡ ማድረጉን ወጣት ጋሻው ይገልፃል። ይህም ሃኪሞቹ እዛ ያለውን የህክምና ቴክኖሎጂ እንዲያዩና ከዚሁ ቴክኖሎጂ ጋር ራሳቸውን እንዲያበቁ እንዳስቻላቸውም ነው የሚጠቁመው። ይህም ድርጅቱ እያደረገው ያለው አንዱ የኮርፖሬት ሃላፊነት መገለጫ መሆኑን ይጠቅሳል።
ድርጅቱ በህክምና ጉዞ ማማከር አገልግሎት ውስጥ ያለ እንደመሆኑ በቀጣይ የውጭ ሀገር ህክምና የሚፈልጉ ታካሚዎችን ማገልገሉን አጠናክሮ ይቀጥልበታል። ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ በመጣው የህክምና ባለሙያ ሀብት ላይ በርካታ ስራዎችን የመስራት ውጥን አለው። ከነዚህም ውስጥ አንዱ ወጣት ተመራቂ የህክምና ባለሙያዎችን ወደ ውጭ ሀገር በመላክና አስተምሮ በማብቃት ወደሀገራቸው ተመልሰው ዜጎችን እንዲያገለግሉ ነው።
በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች በርካታ ችግሮች አሉ። ችግሮች ከሚታዩባቸው ዘርፎች ውስጥ ደግሞ አንዱ የጤናው ዘርፍ እንደመሆኑ በዚህ ላይ ወጣቶች ችግር ፈቺ የስራ ፈጠራዎችን ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመሆኑም በተለይ አዳዲስ ተመራቂ የህክምና ባለሙያዎች እውቀታቸው ለዜጎች አስፈላጊ ነውና ነገ ዛሬ ሳይሉ በህክምናው ዘርፍ ያለውን ችግር በስራ ፈጠራ እንዲፈቱ ይጠበቃል። ለዚህም የመንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው። ሰላም!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2015