ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን ትናንት ካቀረቧቸው ዘገባዎች መካከል የታይላንዱ ንጉስ ዜና አንደኛው ነው፡፡ አልጀዚራ እና ቢቢሲ በድረገፃቸው እንዳስነበቡት ከወደ ታይላንድ የተሰማው አስደሳች ዜና እንደሚያመለክተው፤ የታይላንዱ የ66 ዓመቱ ንጉስ ማሃ ቫጂራሎንግኮርን የግል ጠባቂያቸውን በማግባት ንግስት አድርገዋቸዋል፡፡
ይህ ዜና በልዑላውያኑ ጋዜጣ ታትሞ ይፋ ሲሆን፤ ብዙዎችን አስገርሟል ተብሏል፡፡ የጋብቻ ስነስርዓቱም በንጉሱ ትዕዛዝ በአገሪቷ የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሰፊ ሽፋን አግኝቷል፡፡ ታሂ ቴሌቭዥን ጄነራል ሱዚዳ ቫጂራሎንግኮርን በአገሪቷ ባህል መሰረት ለንጉሱ ሲሰግዱ እና አበባ እንዲሁም የተለየ እንጨት ሲሰጡ ታይቷል፡፡ማምሻውን የፊርማ ስነስርዓቱም የታየ ሲሆን፤ የጄነራሏ ስም ተቀይሮ ንግስት ሱዚዳ ተብለዋል፡፡
የራማው 10ኛ ንጉስ የሚባሉት ቫጂራሎንግኮርን ንግስናቸውን ያገኙት በጥቅምት 2016 የ70 ዓመቱ አባታቸው ባሁም አዱላይዴድ በመሞታቸው ነው::
አንዳንድ የንጉሣዊ ታዛቢዎችና የውጭ መገናኛ ብዙሃን ጄነራል ሱዚዳ ከንጉሱ ጋር የፍቅር ግንኙነት አላቸው ብለው ቢናገሩም፤ ከዚህ በፊት ግን ቤተ መንግሥቱ በመካከላቸው ግንኙነት አልነበራቸውም ብሏል፡፡
ንጉሱ በታህሳስ 2016 የአሁኗን ንግስት የግል ጠባቂያቸው አድርገው የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ የሰጧቸው ሲሆን፤ በመጨረሻም የልዑ ላውያን ቤተሰብ በማድረግ ስማቸው ንግስት የሚል መጠሪያ እንዲታከልበት አድርገዋል፡፡
በሰርጉ ላይ ትልልቅ የአገሪቷ ባለስልጣናት የተገኙ ሲሆን፤ ከ2014 ጀምሮ የአገሪቷ የጦር ሃይል መሪው ፕራይሆን ቻንኦቻ፣ የልዑላዊ ቤተሰቡ አባላትና የቤተመንግስቱ አማካሪዎች ተገኝተዋል
ንጉሱ ሶስት ጋብቻዎችን የፈፀሙ ሲሆን፤ ከሁሉም ጋር ፍቺ ፈፅመዋል፡፡ እ.አ.አ. በ2014 ከአብራካቸው የተገኘ አንድ ወንድ ልጅ እንዳላቸው ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011
ምህረት ሞገስ