በህንድ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻ ኦሪሳ በተባለው የህንድ ግዛት ነፋስ የቀላቀለ ከፍተኛ ዝናብ ሊጥል መቃረቡን የሚትሮሎጂ ትንበያ ማመላከቱን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ለቀው እየወጡ ነው፡፡
ፋኒ ተብሎ የሚጠራው በዚሁ አውሎ ንፋስ ከህንድ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻዎች ወደ ኦሪሳ ግዛት እየተጠጋ መጥቷል፡፡ አደጋው የመሬት መንሸራተት ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
በሰዓት 200 ኪሎ ሜትር እየፈጠነ ያለው ይኸው አውሎንፋስ በነዋሪው ላይ ሊያደርሰው የሚችለውን አደጋ ለመታደግ የአገሪቱ ባለስልጣናት በአካባቢው የሚገኙ ሁለት ወደቦች ስራ እንዲያቆሙና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን ለቀው ወደሌላ አካባቢ እንዲሰፍሩ ማድረጋቸውን ተገልጿል ፡፡
ከአደጋው ጋር ተያይዞ 800 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ከባህር ዳርቻው እንዲወጡ የማድረግ ስራ የተጀመረ ሲሆን አንድ መቶ ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች አውሎንፋሱ ይጠነክራል ከተባለበት ከኦሪሳ ግዛት ይወጣሉ ተብሏል፡፡
በዚሁ ግዛት 858 አመት እድሜ ያስቆጠረ የአምልኮ ስፍራ ህንፃ ጉዳት ይደርስበታል የሚል ስጋት በባለስልጣናቱ በኩል መኖሩን የዘገበው ቢቢሲ በግዛቲቱ የሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች መዘጋታቸውንም ጠቁሟል ፡፡
የሕንድ ምስራቃዊ ዳርቻ ባለፉት 30 አመታት ለአራት ጊዜ ያህል በአውሎ ንፋስ ተመትቷል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011
በየትናየት ፈሩ