የተወለዱት ሐረር ቢሆንም እድገታቸው አዲስ አበባ ነው:: ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደጅአዝማች ወንድይራድ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀመሩ:: በትምህርታቸው እጅግ ታታሪና በጣም ጎበዝ ተማሪ ስለነበሩ ከክፍል ብቻ ሳይሆን ከሴክሽን አንደኛ በመውጣት ራሳቸውን ቤተሰባቸውን ብሎም ትምህርት ቤታቸውን የሚያኮሩ ነበሩ::
የዛሬ የሴቶች ዓምድ እንግዳችን ፕሮፌሰር ወርቅአበባ አበበ:: ለብዙዎች አብነት የሚሆነውን የሕይወት፣ የትምህርትና የሥራ ልምዳቸውንም አካፍለውናል:: ፕሮፌሰር ወርቅአበባ በአሁኑ ወቅት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የሕጻናት ሕክምና ስፔሻሊስት በመሆን እያገለገሉ ሲሆን ከባለቤታቸው ከፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ ጋር በመሆን ላስተማረችን አገራችንና ወገናችን ምን እናድርግ? በማለት “ሪናሰንት የአዕምሮ ጤና እና የሱስ ተሐድሶ ማዕከል “በማቋቋም እየሠሩም ነው::
“……አንደኛና ሁለተኛ ክፍል ትምህርቴን ስድስት ኪሎ አካባቢ ነው የተማርኩት፤ ከዛ በኋላ ግን ደጃዝማች ወንድይራድ በሚባለውና ኮተቤ አካባቢ ባለው ትምህርት ቤት ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን እስካጠናቅቅ ድረስ ቆይቻለሁ” ይላሉ::
ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ወርቅአበባ ገና ትምህርትን ሀ ብለው ሲጀምሩት ስለነበሩ ውጤታቸውም ጥሩና ቤተሰብም ትልቅ ትኩረትና ተስፋ የሚጥልባቸው ታዳጊ ነበሩ:: በጓደኞቻቸው ዘንድም ከጉብዝናቸው የተነሳ “ቀለሜ ” እየተባሉ ይጠሩ የነበረ ሲሆን በተለይም አባታቸው ገና አያያዛቸውን አይተው በመደሰት “የኔ ልጅ ጎበዝ ናት ዶክተር ሆና ዶክተር ነው የምታገባው” እያሉ እንዳሳደጓቸውም ይናገራሉ::
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ፕሮፌሰር ከበታቻቸው ላሉ አምስት እህትና ወንድሞቻቸው ማሳያ (ሞዴልም) የመሆን ኃላፊነት ተጥሎባቸው ስለነበር በትምህርት ቀልድ አያውቁም:: እናትና አባታቸው እንደውም ሌሎቹን ልጆቻቸውን ለምንድን ነው እንደሷ ጎበዝ መሆን ያቃታችሁ? በማለት ይቆጡም እንደነበር ያስታውሳሉ::
ፕሮፌሰር ወርቅአበባ በተለይም በትምህርት በኩል ያለው ትጋታቸው በውጤት የታጀበም ስለነበር በዚህም የስምንተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና (ሚኒስትሪን) መቶ በማምጣት ትምህርት ቤታቸውን ያስጠሩ ቤተሰባቸውንም ያኮሩ ጀግና ሴት ተማሪ ነበሩ:: ይህን ውጤት አስጠብቀው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያለአንዳች መዘናጋት በመማራቸው የ 12 ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በጥሩ ውጤት በማለፍ ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋም ገቡ::
በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ሲከታተሉ የአቻ ግፊት የሚባለውን ነገር እንዲሁም ሴትነትን እንዴት አለፉት? ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱም”……እንደነገርኩሽ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ሙሉ ትኩረቴ ትምህርቴ ላይ ነበር ፤ ሌላ የማየውም ሆነ የምፈልገው ነገር ብዙም አልነበረም፤ ጓደኞቼም ጎበዝ የሆኑና ከፍ ያለ የቤተሰብ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሴቶች ስለነበሩ አልባሌ ቦታ ለመዋል ሁላችንም አናስብም፤ አሁን እንማርና ሌላውን ነገር ደግሞ በጊዜው እናደርገዋለን የሚልም አቋም ነበረን፤” ይላሉ::
በወቅቱ ከፍ ያለ የእግር ኳስ ፍቅር ነበረኝ የሚሉት ፕሮፌሰር ወርቅአበባ ከትምህርታቸው በመቀጠል እጅግ ይዝናኑበት እንደነበርና በዚህም ከትምህርት ቤት እግር ኳስ ጨዋታ ጀምሮ የአፍሪካና የዓለም ዋንጫዎችን ቁጭ ብለው ይመለከቱ እንደነበር ይናገራሉ::
በወቅቱ የ12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈትኖ ትልቅ ነጥብ ያመጣ ተማሪ ይመደብ የነበረው ሕክምና ላይ ነበር:: ፕሮፌሰር ወርቅአበባም የ12ተኛ ክፍል ውጤታቸው ትልቅ ስለነበር ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዲሲን ለመማር መርጠው ገቡ::
“……በነገራችን ላይ ከልጅነቴ ጀምሮ “አንቺ ዶክተር ነሽ” ተብዬ ስላደኩ ሌላ የምመርጠው የትምህርት ዓይነት አልነበረም፤ እጅግ ዶክተር መሆን እፈልግ ነበር:: አሁን ላይ እንኳን ሕክምና ባትማሪ ምን መሆን ነበር የምትፈልጊው ብትይኝ መልስ የለኝም:: እናም አሁን ላይ ሳስበው ምርጫዬ ትክክል ነበር እላለሁ” በማለት ይናገራሉ::
በወቅቱ እሳቸው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለመሄድ ሲዘጋጁ አባታቸው ይታመማሉ፤ ስለዚህ ፕሮፌሰርን ዩኒቨርሲቲ የማድረስ ኃላፊነት የእናታቸው ሆነ፤ ነገር ግን እናታቸው ከእሳቸው በታች ያሉት አምስት ልጆች እንዲሁም የታመሙት ባለቤታቸውን ጥለው ጅማ ድረስ መሄድ አልቻሉም:: ይህንን ሁኔታ የተረዱት ጎበዟ ተማሪ በቆራጥነት አታስቡ እኔ እሄዳለሁ ብለው ተነሱ፤ ምንም እንኳን ጓደኞቻቸው ሁሉ ከቤተሰብ ጋር ቢሆኑም ግባቸውን አሻግረው ያዩት የዛሬዋ ፕሮፌሰር ግን ብቻዬን እሄዳለሁ ብለው ወደማያውቋት ጅማ ተጓዙ::
“……በወቅቱ ከቤተሰቦቼ ጋር መለየቱ ቢከብደኝም፤ አማራጭ አልነበረኝም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጅማ ሄጄ መማሬ ስለሕይወት፣ ስለ አገር ፍቅር ያየሁበት አዕምሮዬም ሰፋ አድርጎ እንዲያሰብ ያደረገኝ ብቻዬን መቆም እንደምችል የተማርኩበት በመሆኑ በጣም ደስ ይለኛል” ይላሉ::
ፕሮፌሰር ወርቅአበባ ከልጅነታቸውም ጀምሮ ዩኒቨርሲቲ መግባት ይመኙ ስለነበር የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጊቢን በጉጉት ነበር ያዩት፤ የመጀመሪያውን ዓመት ጓደኛም ለማግኘት አገሩን ጊቢውን ለመልመድ ጊዜ ቢወስድባቸውም የመጀመሪያውን ዓመት ካጠናቀቁ በኋላ ግን እጅግ በጣም ደስተኛ የሚያደርጋቸው ደስታቸውም እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ አብሯቸው እንዲቆይ ያስቻለ ጓደኛን በማፍራታቸው የጅማ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ቆይታን አብዝተው ይወዱታል::
“…..ዩኒቨርሲቲ መግባቴ እጅግ በጣም ቢያስደስተኝም አካባቢውን ሕይወቱን መልመድ ነበረብኝ:: ለምሳሌ እኔ በግዜ ተኝቼ ጠዋት መነሳት ነው የለመድኩት፤ ዩኒቨርሲቲ ግን እንደዛ አይደለም ማደሪያው የአምስት ሰው በመሆኑ አንቺ ስተተኚ ሰዎች ከውጭ ይገባሉ መቀስቀስ ይኖራል፤ ሌላውና ከባዱ ነገር ደግሞ አባቴ የመጀመሪያውን መንፈቅ ዓመት ትምህርት ሳላጠናቅቅ በሕይወት ማለፉም ነበር:: በጠቅላላው የመጀመሪያው ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ጥሩ አልነበረም” በማለት ጊዜውን ያስታውሳሉ::
ፕሮፌሰር ወርቅአበባ ሁለተኛ ዓመት ላይ ሲደርሱ ግን ታሪክ ተቀየረ፤ ትምህርቱንም ግቢውንም በእጅጉ እየወደዱት መጡ፤ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት አጋር የሚሆናቸው እስከ አሁንም በትዳር አብረው ዘልቀው ቤተሰብ የመሠረቱበትን ጓደኝነት ማግኘት በመቻላቸው ነው:: ፕሮፌሰር ሰለሞን የሦስተኛ ዓመት እሳቸው ደግሞ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ናቸው እናም ጓደኝነት መሠረቱ ይህ ጓደኝነታቸው ደግሞ በተለይም ለፕሮፌሰር ወርቅአበባ ጥሩ ዕድልንም ይዞ የመጣ ነው:: ምክንያቱ ደግሞ ከጓደኛቸው ጋር የማጥናት የመረዳዳት የግቢውን ሕይወት ይበልጥ የመረዳት ዕድልን ፈጠረላቸው:: ይበልጥ በትምህርታቸው ውጤታማ እየሆኑ ስለመሄዳቸው ደግሞ ይናገራሉ ::
ፕሮፌሰር ወርቅአበባ ከልጅነታቸው ጀምሮ ሴት ልጅ ትምህርቷን ዳር ሳታደርስ የወንድ ጓደኛ መያዝ የለባትም የሚል አቋም የነበራቸው ቢሆኑም ሁለተኛ ዓመት ሆነው ለተፈጠረው ጓደኝነት ከዛም የፍቅር ጥያቄ ግን እምቢ የማለትን አቅም አጡ:: ጥያቄውንም አስበው አውጥተው አውርደው ላለመቀበል የሚያስችል ምክንያት ስላላገኙ ተቀበሉት::
“…..በሕክምና የሁለተኛ ዓመት በጣም ከባድ የሚባል ነው:: ነገር ግን ጓደኛዬ በዚህ ሂደት አልፎ ሦስተኛ ዓመት የደረሰ በመሆኑ ለእኔ ብዙ ነገሮችን አቅሎልኛል፤ እዚህ ላይ ግን ሁኔታው አይጎዳም ማለት አይቻልም፤ ብዙ ሰዓትን ከጥናት ውጪ ሆኖ ማሳለፍ ይኖራል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጥንቃቄ ያልታከለበት ግንኙነት ከሆነ ጉዳቱ ትምህርትንም የሚያስተጓጉል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በጥንቃቄ ከተያዘ የሕይወት ረዳት እንደማግኘት ነው” ይላሉ ::
ፕሮፌሰር ጓደኛቸው ከእሳቸው በአንድ ዓመት ቀደም ያሉ መሆናቸው ይህንን እንደዚህ አጥኚው ፤ ይህ መጽሐፍ ለዚህ ትምህርት ይረዳሻልና አንብቢው፤ መምህራኖቹ የሚፈልጉት ይህንን ነው፤ እንደዚህ ማድረግሽ ወጤታማ አያደርግሽም የሚል ምክርና እርዳታን እያገኙ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን ከፍ ባለ ውጤት አጠናቀቁ::
ፕሮፌሰር ሰለሞን ቀድመው ተመርቀው ነበር፤ እሳቸው ደግሞ የተግባር ልምምድ ላይ ናቸው፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ መራራቁ ሊመጣ ስለሆነ ለምን አንጋባም የሚል ሀሳብ ከፕሮፌሰር ሰለሞን ቀረበ፤ ፕሮፌሰር ወርቅአበባም ቢያንስ ጥንድ ሆነው አብረው ለመመደብ አልያም በቅርብ ርቀት አብረው ለመሥራት በማሰብ ገና የሥራ ላይ ልምምድ ውስጥ ሆነው ትዳር መሠረቱ::
“…..እናቴ የሐረር ሰው ስለሆነች ያን ያህል ወግ አጥባቂ የምትባል አይነት አይደለችም፤ ያም ቢሆን ግን እኔም እስከዛ ድረስ ጓደኛ እንዳለኝ ማንም አያውቅም፤ ሆኖም ከጓደኛዬ ጋር የመጋባት ሃሳቡን ስናስብ እነሱንም ማለማመድ ጀመርኩ፤ ኋላም ያለውን ነገር በመናገር ሽማግሌ ይላክ ብለን ስንጠይቅ እናቴ ሳትመረቂ ሽማግሌ አልቀበልም ነገር ግን እናንተ ያመናችሁበትና የምትፈልጉት ከሆነ ያሰባችሁትን አድርጉ በማለት ፍቃዷን ሰጠችን፤ እኛም ከእኔ ሁለት ከእሱም ሁለት ሰው ይዘን አምባሳደር በመሄድ ተፈራረምንና ተጋባን” በማለት ይናገራሉ::
የዛሬ 27 ዓመት በዩኒቨርሲቲ የተጀመረው ጓደኝነትም 22ቱን ዓመት በትዳር አሳምሮ በሁለት ልጆች ተባርኮ እዚህ ደርሷል:: በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ደግሞ ፕሮፌሰር ወርቅአበባ ሥራንና ትምህርትን ብሎም ልጆች ወልዶ ማሳደግን ጎን ለጎን እያስኬዱ ፕሮፌሰርነት ደረጃ ላይ ደርሰዋል::
ፕሮፌሰር ወርቅአበባ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ ቡታጅራ ተመድበው ለአራት ዓመት ከሠሩና የመጀመሪያ ልጃቸው ከወለዱ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሕጻናት ሕክምና ዘርፍ ትምህርታቸውን ቀጠሉ:: የዩኒቨርሲቲው የሥራ ባልደረባም የመሆን ዕድልን አገኙ::
“…..አሁን ትምህርት ከልጅ ጋር ነው ይህ ሁኔታ ደግሞ ትንሽ ከበድ ይላል፤ ነገር ግን ልጅ ስለተወለደ መማር አይቻልም ማለት ደግሞ ስህተት ነው:: በመሆኑም አጣጥሞ መምራት ያስፈልጋል:: እኔ ዕድለኛ ሆኜ በትምህርትም በሥራም ከዛም ልጅ ወልዶ በማሳደጉ ላይ ባለቤቴ ከፍተኛ የሆነ እገዛን ያደረገልኝ፤ በዚህም ለታላቅ ውጤት በቅቻለሁ” በማለት ሁኔታውን ይናገራሉ::
ሴቶች ውጤታማ መሆን አለብን ካልን ትልቁና አስፈላጊው ነገር የራሳችን ቁርጠኝነት ሊኖር ይገባል፤ የሚሉት ፕሮፌሰር ወርቅአበባ ልጅ ወልጃለሁና በቃኝ የምንል ከሆነ የእኛ መኖር እዛ ጋር ያከትማል ነገር ግን መማር አለብኝ መሥራት እችላለሁ ብሎ ለሚነሳ ደግሞ የማይቻል የለም ይላሉ::
“……እኔ እስከ አሁንም የማደርገው ነገር በቢሮ ውስጥ መሥራት ያለብኝን ነገር በሙሉ ቢሮ ጨርሼ ለመሄድ ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ፤ ከዛ የሚተርፍ ከሆነ ደግሞ ልጆቼ ሲተኙ እየራለሁ:: ይህንን የማደርገው ሥራዬም ልጆቼም እኔ ስለማስፈልጋቸው ሁለቱንም ለማቻቻል በማሰብ ነው” ይላሉ::
የትኛዋም ሴት በሕይወቷ ልትደርስበት የምትፈልገውን ግብ ላይ ለመድረስ ጠንክራ መሥራት ብቻ ነው ከእሷ የሚጠበቀው፤ ራስን ለዓላማ አስገዝቶ ትኩረት አድርጎ መሥራት ከተቻለ የሚፈለግበት ደረጃ ይደረሳል፤ የሚሉት ፕሮፌሰር ወርቅአበባ እሳቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ትምህርታቸውን እንደ ግብ አስቀምጠው በመሄዳቸው ለዚህ መብቃታቸውን ይናገራሉ::
“……መጀመሪያ የተማርኩት የሕክምና ሙያ በቃኝ ብዬ ብቀመጥ እችላለሁ ሊያኖረኝም ይችላል፤ ነገር ግን በየጊዜው ሙያን ማሳደግ ራስንም ትምህርቱንም ዋጋ መስጠት በመሆኑ ከነበርኩበት ስፔሻላይዝድ ለማድረግ ትምህርት ቤት ገባሁ፤ ቀጥሎም ሰብ ስፔሻሊቲ ስማር የተሻለ የሚያደርገኝን በተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ ትምህርቴ እንዲያጠነጥን መረጥኩ ሌሎች ለጥናትና ምርምር የሚረዱኝን ኮርሶች በአገር ውስጥ በአሜሪካና ካናዳ ተምሬያለሁ፤ በዚህም ጥናትና ምርምሮችን ማድረግ ቻልኩ፤” በማለት ስለትምህርት አካሄዳቸው ይናገራሉ::
በእኛ አገር እምብዛም ክትትሉ ስለሌለ ነው እንጂ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሆኖ በአንድ ደረጃ ላይ ረጅም ጊዜ መኖር አይፈቀድም የሚሉት ፕሮፌሰር ወርቅአበባ አንድ ሰው ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆኖ የሚቆይበት ጊዜ ገደብ አለው፤ በመሆኑም እሳቸውም ተባባሪ ፕሮፌሰር ከሆኑ በኋላ ጊዜውን ጠብቀው ወደ ሙሉ ፕሮፌሰርነት ደረጃ መሻገራቸውንም ይናገራሉ::
ባለ ብዙ ራዕይ ፕሮፌሰር ወርቅአበባ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በሙያችን ለአገራችን ምን እናድርግ ብለው ሲያስቡ ያገኙት ምላሽ ለብዙዎች መጥፋት ቤተሰብ መበተን ለአገር ኢኮኖሚያዊ ውድቀት ምክንያት እየሆነ በመጣው የሱሰኝነት ችግር ላይ አንድ ነገር ለምን አንሠራም በማለት ተስማምተው ሥራውን ለመጀመር ተነሱ:: ይህ በወቅቱ ቀላል ባይሆንም ዘውዲቱ ሆስፒታል ተፀንሶና በትንሹ ተጀምሮ ዛሬ ላይ የብዙዎች ተስፋ የሆነ ማዕከል ለማቋቋም አስችሏል::
ከዘውዲቱ ሆስፒታል ከወጡ በኋላ ይህንን ሀሳባቸውን መሬት ለማስያዝ ሌላ አማራጭን ማማተር ጀመሩ፤ ያገኙት ነገር ግን ለመኖሪያ ቤትነት እየሠሩት ያለውን ቤት ወደሕክምና ማዕከልነት መቀየርን ነው:: ከባለቤታቸው ጋር ተስማምተው ገቡበት::
” ……ቤቱን በራሳችን አቅም ጨርሰን ሬናሰንት የአዕምሮ ጤና እና የሱስ ተሐድሶ ማዕከል ለማድረግ ብዙ ለፍተናል፤ ዛሬ ላይ ግን ልፋታችን ፍሬ አፍርቶ ሳየው እንኳንም ወሰንኩ እላለሁ፤ አሁን ላይ ሳያስቡት በተለያዩ ሱሶች ውስጥ ወድቀው እየተሰቃዩ የነበሩ ወጣቶችና ቤተሰቦቻቸው እፎይታን አግኝተዋል፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ለእኔ ደስታን ፈጥሮልኛል” ይላሉ::
የትኛዋም ሴት ብትሆን ሕልም አላት ግን ደግሞ ራቅ አድርጋ ያሰበችውን ብቻ ሳይሆን ዛሬ ላይ በደረሰችበት ስኬትም መደሰት እሱን ማጣጣም አለባት:: ይህንን ስታደርግ ያ እሩቅ ያለው ሕልሟም የማይቀርብበት ሁኔታ አይፈጠርም ይላሉ::
“…..በየዕለቱ የምሠራው ሥራ ውጤታማ ሲሆን ሕልሜ ሞልቷል እላለሁ፤ ለምሳሌ ድሮ ስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ተፈትኜ መቶ ሳመጣ ለወቅቱ ሕልሜ ሞልቶ ነበር፤ በኋላም ማትሪክ ተፈትኜ ዩኒቨርሲቲ ስገባም እንደዛው የመጀመሪያ ሁለተኛ ከዛም አልፎ እስከ ፕሮፌሰርነት ደረጃ ድረስ እስክደርስ ድረስ ያሉት ቀናቶች በሙሉ ሕልሜ እውን የሆነባቸው ናቸው:: በመሆኑም ሰዎች በተለይም ሴቶች የእኔ ሕልም ያ ነው ብለው አርቀው አስቀምጠው ዛሬን ሳያጣጥሙ ማለፍ የለባቸውም” በማለት ይመክራሉ::
ዛሬ ባለኝ ነገር ደስተኛ ነኝ፤ ነገ ለሚሆነው ደግሞ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ:: ነገር ግን ሁሌም ሕልም ስለማይሞላ መጨነቁ ዋጋ ያስከፍላል:: በመሆኑም እያንዳንዳችን በሙያችን የራሳችን ዓለም ስላለን ዛሬ የቆምንበትን በደንብ እየፈተሽን ነገር ደግሞ የተሻለ ለማድረግ እያለሙ መሄድ አስፈላጊ ነው::
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2015