አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ህፃናት ከውጭ ድጋፍ ነፃ የሆነ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ አሁን ባለንበት አስቸጋሪ ሁኔታ በፍፁም ሊታሰብና ሊደረስበት የማይችል ይመስላል:: የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ግን ሕብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ከተባበሩኝ በቀላሉ ልደርስበትና ላሳከው የሚያስችለኝን ተግባር በቁርጠኝነት እየሰራሁ ነው ይላል::
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት መሻሻል መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዮሐንስ ወጋሶ እንደሚሉት በእርግጥ በገጠር የሚኖረው ከ85 በመቶ ሕብረተሰብ አሁንም የውሃና ኤሌክትሪክ አገልገሎት ተደራሽ አይደለም:: አሁንም አብዛኛው የገጠር ሕብረተሰብ በተለይም እማወራዋ በየቀኑ ውሃ ለመቅዳት ከሦስት እስከ ስምንት ሰዓት ረጅም ጉዞ ትጓዛለች:: ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ልጆች በውሃ መቅዳቱ እየተሳተፉ እናታቸውን ስለሚያግዙ ለትምህርት የሚተርፍ ጊዜ አይኖራቸውም:: ትምህርት ቤት ባቅራቢያቸው ቢኖርም ውሃ ባለማግኘታቸው ብቻ እንኳን ወደ ትምህርት ቤት ላይመጡ ይችላሉ::
ጥቂት ሕዝብ በመጨናነቅ ወደሚኖርባቸው ከተሞች ሲመጣ ደግሞ ወላጅ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ሊልክባቸው የማይችልባቸውና ልኳቸውም በየትምህርት ቤቱ ጥራት ያለው ትምህርት ሊያገኙባቸው የማያስችሉ በርካታ ችግሮች አሉ:: አንዱ ወላጅ አንድ እንቁላል 15 ብር፤ አንድ ዳቦ አምስት ብር ገዝቶ ልጁን ቁርስ በማብላት ወደ ትምህርት ቤት የሚልክበት አቅም የሚያሳጣ የኑሮ ውድነት ሊሆን ይችላል::
ትምህርት ሚኒስቴር እንደ አገር ባደረገው ግምገማና ጥናት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች በከተማም ሆነ በገጠር ተመሳሳይነት ያላቸው ቢሆንም በተለይም በገጠሩ ልጆች አንደኛ ክፍል በሚገቡበት ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት ስለማይሄዱ ቢሄዱም ወላጆች በአግባቡ መግበውና ጤናቸውን ጠብቀው ማስቀጠል ላይ ችግሮች ስላሉ ፤ በትምህርት ቤት የሚሰጣቸው የትምህርት አገልግሎት ውጤታማ እንዳይሆን ስለማድረጉ ይናገራሉ::
እንደ አቶ ዮሐንስ ትምሀርት ሚኒስቴር ከዚህ ችግር ተነስቶ ችግሮቹ የሚፈቱበትን የመፍትሄ አሰራሮች ዘርግቷል:: በቅርቡ በአዲስ መልክ ያስጀመረው ብሔራዊ የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ መርሐ ግብርም ለተጓደለው የትምህርት ጥራትም ሆነ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት የማይመጡበትን ችግር በዘለቄታው ለመፍታት መፍትሄ የሚሰጥ አሰራር ሆኖ መቀመጡን ያብራራሉ::
አሰራሩ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርንና ጤና ሚኒስቴርን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ነው:: ሁሉም በትምህርት ጉዳይ መሳተፉና ያገባኛል ማለታቸው ደግሞ በጋራ የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት ያስችላል:: አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ህፃናት ከውጭ ድጋፍ ነፃ የሆነ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ የሚቻለውም በዚሁ መንገድ በቅንጅት መሥራት ሲቻል እንደሆነም አቶ ዮሐንስ ያስረዳሉ::
ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ለውጥ ለማምጣት ከሚተጉት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኢማጂን ዋን ዴይ ( Imagin1Day ) ሲሆን የድርጅቱ የስትራቴጂክ ትብብር (ፓርትነር ሺፕ) ዳይሬክተር አቶ ያሳቡ ብርቅነህ እንደሚያብራሩት ድርጅቱ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2030 ሁሉም ህፃናት ከውጭ ድጋፍ ነፃ የሆነ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ የማድረግ ዓላማን አንግቦ ወደ ሥራ ከገባ 16 ዓመታትን አስቆጥሯል::
በዚህ ጊዜ ውስጥ ንቅናቄ ከመፍጠር ጀምሮ ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በ2030 አሳካለሁ ብሎ ላስቀመጠው ግብ መዳረሻ የሚሆኑ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ችሏል:: በሥራው የወረዳና ዞን ትምህርት አመራሮች፤ የወላጅ መምህር ህብረት (ወተመ) ይሳተፋሉ:: ‹‹ያለ ሕብረተሰቡ ተሳትፎ ዕቅዳችን ግቡን መትቶ ለስኬት ልንበቃ አንችልም›› የሚሉት ዳይሬክተሩ በጦርነትም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ የሚሰሩት የልማት ሥራ አሉ:: ከህብረተሰቡና ከሌሎች
ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ማድረግ ሌላው የድርጅቱ ተግባር ነው:: በጦርነትና በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን መጠገን፤ የወደሙትንም መልሶ መገንባትም ከሥራዎቻቸው መካከል እንደሚገኝበት ያስረዳሉ::
ደብተር፤ እርሳስ፤ እስኪሪብቶን ጨምሮ ህፃናት እየተጫወቱ የሚማሩባቸው የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችንና ግብዓቶችም ይቀርባሉ:: በተለይ ቀውስ ባለባቸው አካባቢዎች ሴት ተማሪዎች የጥቃት ሰለባ ይሆናሉ የሚሉት አቶ ያሳቡ ጥቃትን የሚከላከል የስርዓተ ጾታ ክበባትን በየትምህርት ቤቱ የማቋቋም፤ ጥቃቱ ለደረሰባቸውም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የስነ ልቦና ድጋፍ ማድረግ ፤ የፍትህና የሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ይሰራሉ::
እናቶች በችግር ምክንያት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሳይልኩ እንዳይቀሩ ሴት ተማሪዎችን በተለያየ መንገድ በመደገፍና የውሃ አገልግሎት በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች እንደ ገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በመፍጠር ከችግራቸው እንዲላቀቁ ከማድረግ ባሻገር ለሴት ተማሪዎች ንጽሕና መጠበቂያ ሞዴስ፤ ውሃ፤ የመታጠቢያና ልብስ መቀየሪያ እንዲሁም ማረፊያ ክፍሎች መገንባትን ድርጅቱ የሰራቸው ስራዎች መሆናቸውን ያብራራሉ::
ዳይሬክተሩ አቶ ያሳቡ እነዚህ ተግባራት የተከናወኑባቸው አካባቢዎችን አስመልክተው እንደሚያስረዱት በአማራ ክልል ደሴ ላይ ሕይወት ፋና ትምህርት ቤት ተጠቃሽ ነው:: ተውለደሪ ወረዳ ጃሪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ ሌላው ተጠቃሚ ሲሆን ሰሜን ወሎ ቆቦ ወረዳ ሮቢት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በድርጅቱ ድጋፍ ካገኙት መካከል ይጠቀሳሉ::
በጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸው ጋር በተያያዘ ባከናወኗቸው ሥራዎች ተጠቃሚ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል የጦርነት ቀጠና የነበረችው ጋሸና ትገኝበታለች:: አቶ ያሳቡ እንደተናገሩት ጋሸና ውስጥ አርቢት ወረዳ ላይ ‹‹መለ›› የሚባል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገንብቶ ለአገልግሎት ውሏል:: በኦሮሚያ ክልል ባሌ ውስጥ እንዲሁም ባቢሌ ላይ ትምህርት ቤት ከመገንባት ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን መሥራታቸውን አውስተዋል::
‹‹ድርጅቱ በርካታ ሥራዎችን በስድስት ክልሎች ሰርቷል›› የሚሉት ዳይሬክተሩ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ለትምህርት ሚኒስቴር፤ ለየክልሉ ትምህርት ቢሮዎች ማስረከባቸውንም ያብራራሉ:: ድርጅቱ ሥራውን ትግራይ ክልልን ጨምሮ ደቡብና ኦሮሚያ ላይም የተጎዱ ትምህርት ቤቶች ተጠግነዋል፤ የልጃገረዶች ንጽሕና መጠበቂያ ክፍሎች ተገንብተዋል፤ የውሃ አገልግሎት ጥገና ተሰርቷል፤ ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን የተጎዱ የመማሪያ ክፍሎች ታድሰዋል::
‹‹ በጦርነቱ ምክንያት በተጎዱ አካባቢዎች ላይ ትምህርት ተቋማቱ ከመውደማቸውም በላይ ወላጆች ለህፃናት ተማሪዎቻቸው ቋጥረው የሚልኩት ምግብ የለም›› በዚህ ምክንያት አካባቢዎቹ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሲደገፉ መቆየታቸውን አሁንም እየተደገፉ መሆኑን ይናገራሉ:: አቶ ያሳቡ ድርጅታቸው በተለይ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጋር በብርቱ የተቆራኘ ሚና እንዳለውም አውስተው ትምህርት ሚኒስቴር እንደ አዲስ ካስጀመረው ብሔራዊ የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ መርሐ ግብር ጋር ተያይዞ የጎላ ስራን ይሰራል ብለዋል::
እንደ አገር ቅድመ መደበኛ ትምህርት ሦስት ተከፍሎ እንደሚሰራበት ገልጸው የመጀመሪያው ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ሲሆን በዚህም የአንድ ዓመት ትምህርት የነበረው አሁን የሁለት ዓመት ሆኗል:: ሁለተኛው ደግሞ የቅድመ መደበኛና ሌሎች ዕድሎች ያላገኙ ልጆች የሁለት ወር ቅድመ ዝግጅት እንዲኖራቸው ክረምት ላይ የሁለት ወር ትምህርት ተሰጥቷቸው መስከረም ላይ አንደኛ ክፍል የሚገቡበት ነው:: ሦስተኛው ልጆች ለልጆች ሲሆን በየሰፈሩ ከአምስተኛ እስከ ሰባተኛ ክፍል ያሉ ትላልቅ ታዳጊ ልጆችን ማብቃት የተመለከተ ትምህርት መሆኑን ያብራራሉ::
ድርጅታቸው በነዚህ በሦስቱም ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራና በተለይም ልጆች ለልጆች የትምህርት መርሐ ግብር ላይ በአካባቢ ላሉና ለሚደግፏቸው መምህራን በቂ ስልጠና ይሰጣል:: በዚህ መልኩ በሰፈራቸው ውስጥ ሆነው በታላላቆቻቸው የቅድመ መደበኛ መሰረታዊ ትምህርት እንዲያገኙ መምህራን እንዲረዷቸው ይደርጋል:: ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ላይም ትምህርት የሚሰጥባቸውን የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶችን በሥሩ ለሚደገፉ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ያቀርባል:: የሚያቀርባቸው የትምህርት ቁሳቁሶች በሙሉ ህፃናት እየተጫወቱ የሚማሩባቸው ናቸውⵆ
ትምህርታቸውን የሚከታተሉባቸው ሌሎች ቁሳቁሶች፤ የመዝናኛ እና፤ የመማርያ አቅርቦቶችን ያመቻቻል ምቾት የሚሰጧቸውን ክፍሎች ይገነባና መምህራኖቻቸውን ያሰለጥናል:: አሁን ላይ አፋር ውስጥ ስራውን አንድ ብሎ የጀመረ ሲሆን ትግራይ፤ ኦሮሚያ፤ አማራ ክልልና ሌሎች ስድስት ክልሎች ላይ ባሉ ትምህርት ቤቶችና የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የልማትና የሰብዓዊነት ሥራዎች በማከናወን በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2030 ዓ.ም ሁሉም የኢትዮጵያ ህፃናት ከውጭ ድጋፍ ነፃ የሆነ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችል ዘላቂ ሁኔታ መፍጠር መሆኑን ደጋግመው ይናገራሉ ፡፡
‹‹በተለይ ቅድመ መደበኛ ላይ መምህራኑ ህፃናትን ማዕከል ያደረገና በጨዋታ ላይ የተመሰረተ ትምህርት እንዲሰጡ ነው የሚፈለገው›› የሚሉት ዳይሬክተሩ ከዚህ አንፃር በድርጅቱ መምህራንን የማብቃትና የማሰልጠን ሥራ ይሰራል:: በተጨማሪም አግባብነት ያላቸው መጽሐፍት እንዲቀርቡ ይደርጋል:: በቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ በሙያው የሰለጠኑ ህፃናት ተንከባካቢ ባለሙያዎች ከማፍራት አንፃር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ መሆኑንም ይናገራሉ:: ከጤና አጠባበቅና ህፃናት አያያዝ አንፃር ስልጠናዎች እንዲያገኙ በቅንጅት ይሰራል::
እንደ አገር የህፃናት ሁለንተናዊ ደህንነትና መብት እንዲሁም ተሳትፏቸው እንዲያድግ የሚያደርግ ስርዓት እንዲኖር በዕድሜያቸው ማወቅ ያለባቸውን እያወቁ እንዲያድጉ አገራቸውን የሚወዱ ጥሩ ዜጋ እንዲሆኑ ለማስቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ ይገኛል::
በድርጅቱ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ስራ አስኪያጅ ሀዊ ዓለሙ እንደሚሉት ድርጅታቸው ከትምህርት ሚኒስቴር ፤ ከህብረተሰቡና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እስካሁን በሰራቸው ሥራዎች እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2030 ዓ.ም ሁሉም የኢትዮጵያ ህፃናት ከውጭ ድጋፍ ነፃ የሆነ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችል መደላድል እየፈጠረ ይገኛል::
ወደ ሥራ ከተገባ ጀምሮ በስድስት ክልሎች ከ946 ትምህርት ቤቶች ጋር የጋራ ቅንጅት በመፍጠር መሥራት ተችሏል:: ከነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 123ቱን ሙሉ በሙሉ ድርጅቱ የገነባቸው ሲሆን ከ175 ሺ በላይ የሚሆኑና የትምህርት አገኝተው የማያውቁ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ህፃናት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ አድርጓል::
ለ453 ሺ በላይ የሚሆኑ ህፃናትም የህፃናት ጥበቃ አገልግሎቶችንና የቅድመ ልጅነት ትምህርት እንዲያገኙ ሆኗል:: 65 የውሃ ተቋማትን እያስገነባ ሲሆን በተለይ የውሃ ተቋማት ሲያስገነባ ውሃ የሚሰጠው ለትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆን ትምህርት ቤቶቹ ላሉበት አካባቢ ጭምር እንደሆነ ይናገራሉ::
‹‹ በማህበረሰብ ውስጥ ውሃ መቅዳት የሴቶች ኃላፊነት በመሆኑ ለትምህርት የሚያውሉትን ጊዜ ይሻማባቸዋል፤ ሴቶቹ ውሃ ለማግኘት ቢያንስ በቀን ከሦስት እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል:: በዚህም ለትምህርት ቤት የሚሆን ሰዓት አያገኙም :: በትምህርታቸው ወደኋላ ይቀራሉ፤ የሴቶች የትምህርት ተሳተፎ ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር ከማይመጣጠንበት ምክንያት አንዱም ይህ ነው» ይላሉ::
በመሆኑም ውሃ ለትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ማህበረሰብ የሚሰጥበት ምክንያት ለዚህ እንደሆነም ነግረውናል:: ሴት ታዳጊ ተማሪዎች የወር አበባቸው በሚመጣበት ወቅት በትምህርት ቤቶች ንጽህናቸውን የሚጠብቁባቸው መታጠቢያ ቤቶችና ውሃ ባለመኖሩ በየወሩ ለአምስት ቀናት ያህል ከትምህርት ቤት ይቀራሉ፤ ነገር ግን ድርጅቱ በሚሰራባቸው ክልሎች ችግሩ እንደተቀረፈም ያስረዳሉ::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም