ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት እየደረሰባት ትገኛለች:: በድርቅ አደጋ በተደጋጋሚ መጠቃት፣ የአፈር ለምነት እየተመናመነ መምጣትና የመሬት መራቆት የአለማችን አሳሳቢ ጉዳዮች ሆነዋል:: የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ተጋላጭነትን ለመቀነስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ዘላቂነት ያለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት አንዱ መሳሪያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ስራን በተጠናከረ መልኩ ማከናወን ነው::
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የረጅም ጊዜ ተሞክሮ እንዳላት ይታወቃል:: ሀገሪቱ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እርከን በመስራት፣ የተለያዩ የዛፍ ችግኞችና እጽዋቶችን በመትከል ባከናወነቻቸው ተግባራት የደን ሽፋኗን መጨመር የቻለችበት ሁኔታ ቢኖርም፣ ውጤቱ አንዴ ከፍ ሲል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ እያለ የደን ሽፋንን በማሳደጉ በኩል ሲከናወን የቆየውን ስራ ዘላቂነት ማረጋገጥ ሳይቻል ቆይቷል:: ይህ ሁኔታም በአፈር መሸርሸር፣ በደን መራቆትና ወራጅ ወንዞች ላይ የሚደርሰው አሉታዊ ተጽእኖ እንዲቀጥል አድርጎታል::
የችግሩ አሳሳቢነት አስቀድሞ የታያቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተነሳሽነቱን በመውሰድ እንደ ሀገር በ2011ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ማስጀመራቸው ይታወሳል:: በዚህም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረውን የተፈጥሮ ሀብት መመናመን በመታደግ አስተዋጽኦ ማበርከት ተችሏል:: በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ለተፈጥሮ ለደን፣ ለምግብነትና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የተለያየ ዝርያ ያላቸውን የዛፍ ችግኞችና እጽዋቶች በመትከል እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል::
ንቅናቄው ጎረቤት ሀገራትንም ባካተተ መከናወኑም ኢትዮጵያ በዓለም በአረንጓዴ ልማት ስሟ እንዲጠራ ከማስቻሉም በላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን ለሽልማት አብቅቷቸዋል:: ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ለስብሰባ በተለያየ ጊዜ ወደ ሀገር የመጡ የሀገር መሪዎችና እንግዶች ጭምር በችግኝ ተከላው በመሳተፍ መርሃ ግብሩ ውጤታማ እንዲሆን አድርገዋል::
ሕዝብን በሰፊው ማሳተፍ የቻለው የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ከአባይ ግድብ ቀጥሎ ተጠቃሽ መሆን ችሏል:: ባለፉት አመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 20 ቢሊዮን የዛፍ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ 25 ቢሊዮን ችግኞች እንዲተከሉ በማድረግ ከእቅድ በላይ አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል::
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የደን ዛፍ ችግኞችንና ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ በአርሶ አደር ማሳ ላይ የሚተከሉ የጥምር ደን እርሻ አካል የሆኑ የፍራፍሬ፣የእንስሳት መኖ እንዲሁም ለማገዶ የሚውሉ የዛፍ ችግኞች ተከላና የከተማ ውስጥ የአረንጓዴ ልማት ስራ ተከናውኗል::
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ 20 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ መሳተፉን መረጃው አመልክቷል:: አረንጓዴ አሻራ ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ረገድም ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከቱንና ከ767ሺ በላይ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸውም ተመልክቷል::
ኢትዮጵያ ለአራት አመታት የተገበረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጠናቅቆ ለሁለተኛው ዙር ደግሞ ዝግጅት እየተደረገ ነው:: ይህ ከ2015 በጀት አመት እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ ባሉት አመታት ‹‹አረንጓዴ አሻራችን ለዘላቂ ልማታችን›› በሚል መሪ ቃል የሚተገበር ይሆናል:: በዚህም በሕዝብ ንቅናቄ ወደ ስድስት ቢሊየን የዛፍ ችግኞች ተከላ ለማከናውን ሀገሪቱ ተዘጋጅታለች::
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከናወኑ ተግባራትን እንዲሁም የሁለተኛውን ምዕራፍ ዝግጅት በተመለከተ ሰሞኑን በሳይንስ ሙዚየም ውይይት ተካሂዷል:: በውይይቱም የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል:: መድረኩ በሳይንስ ሙዚየም ‹‹ከቤተሙከራ ወደ አዝመራ›› በሚል መሪ ቃል ለሕዝብ እይታ ክፍት የሆነው ኢግዚቢሽን አካል መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል::
የውይይት መድረኩ በግብርና ሚኒስቴር ዶክተር ግርማ አመንቴ እና በእለቱ የክብር እንግዳ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በተከፈተበት ወቅት እንደተጠቆመው፤ ያለፈው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ክንውን ተሞክሮ ለሁለተኛው ምዕራፍ ሥራ መሠረት እንደሆነና ለበለጠ ውጤት እንደሚያነሳሳ ተጠቁሟል::
በተቀናጀና በተደራጀ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሰብል ምርታማነት፣በእንስሳት ልማትና በተለያየ የግብርናው ዘርፍ ስኬቶች መመዝገባቸውንና ስኬቶቹም በአርሶ አደሩ ገቢ መጨመር ላይ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ በማስታወስ፣ ለእዚህም የደን መጨፍጨፍና የአፈር መከላት መቀነስን ለአብነት ጠቅሰዋል:: ለአየር ንብረት የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባቱ ስራም መንገድ የከፈተ መሆኑንም አመልክተዋል::
ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ተሞክሮ በመውሰድ የአየር ለውጥ ተጽእኖን ለመቀነስ የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከታቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮዋን እንድታካፍል ኬኒያ በግብርና ሚኒስቴሯ በኩል መጠየቋንም ጠቅሰዋል:: በአረንጓዴ ልማት የተሰራው ሥራ በክፍለ ሀጉሩም ትኩረትን የሳበና ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል:: ኢትዮጵያ በዓለምም እውቅና ያገኘችበት ሥራ እንደሆነ አስታውቀዋል::
ዶክተር ግርማ አመንቴ እንዳሉት፤ በአረንጓዴ አሻራ ክንውን ወቅት ከነበሩት አፈጻጸሞች ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር ከ2015ዓ.ም ጀምሮ ለሚተገበረው ለሁለተኛው ዙር ወይንም ምዕራፍ ግብአት አድርጎ ለመጠቀም መዘጋጀት ይገባል:: በመጀመሪያው ዙር የነበሩት ተግዳሮቶች መታረም ይኖርባቸዋል:: በሁለተኛው ዙር ለሚከናወነው የአረንጓዴ ልማት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ከባለድርሻ አካላት ብዙ መስራት ይጠበቃል፤ በዚህ መድረክ የሚካሄደው ውይይትም ለውጤት ዝግጁ ያደርጋል::
በክብር እንግድነት የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ተንከባክባ ለምርትና ምርታማነት እንዲውል ማድረግ ባለመቻሏ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የግብርና ምርቶችን ከውጭ በግዥ በማስገባት ለአመታት ስትጠቀም ቆይታለች:: መንግሥት ይህን ክፍተት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ወይንም እቅድ በመደገፍ በግብርናው ዘርፍ ሰፊ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል::
ለዚህም አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ይጠቀሳል:: መርሃ ግብሩ ለደንና ለጥምር የእርሻ ሥራ እያስገኘ ካለው ጥቅም በተጨማሪ ለአየር ንብረት ለውጥ ያለውን ተጋላጭነት በመቀነስ፣ የቤተሰብ ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ ለዜጎችም ለኑሮ ተስማሚ የሆነ አካባቢን እንዲሁም የሥራ እድል በመፍጠር፣ ዘርፈ ብዙ ውጤት አስገኝቷል:: መርሀ ግብሩ ዘላቂ ኢኮኖሚ ለመገንባትና የብልጽግና ጉዞን ለማፋጠን የሚያግዝ ሆኖ ተገኝቷል::
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከእቅድ በላይ አፈፃፀም ቢመዘገብም ውጤቱ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተመሳሳይ ነበር ማለት እንደማይቻል የጠቀሱት አቶ አደም፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ምሁራን ተደራሽነቱን በማስፋትና የሚጠበቅባቸውን ተልእኮ በመወጣት ረገድ ብዙ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል::
የአሰራር ሥርአት መዘርጋት፣ በወቅቱ አስፈላጊውን ግብአት በማቅረብ የተሟላና ስኬታማ ተግባራትን መወጣት ይጠበቃልም ብለዋል:: ችግኝ ከመትከል ባለፈ የኢኮኖሚ አማራጮችን በማስፋፋት ለመጪው ትውልድ የለማችና የበለፀገች ሀገር ለማስተላለፍ በሁሉም አካባቢዎች በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል::
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 25 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል መቻሉን በማስታወስ፣ ይህ ተግባር ከአባይ ግድብ ፕሮጀክት ቀጥሎ በልማት ስኬት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል:: ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ፕሮጀክቶች በራሷ የመፈፀም አቅም እንዳላት ማሳያ እንደሆነም አመልክተዋል:: ሕዝቡም የመንግሥትን ጥሪ ተቀብሎ ጉልበቱንና ገንዘቡን በማስተባበር እያደረገ ያለው ተሳትፎም ያስመሰግነዋል ብለዋል::
ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን፣ መንከባከብና የሕይወት መመሪያ አድርጎ መውሰድ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ችግኞች ባለቤትም ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል:: ሕዝብን አስተባብሮ መሥራት ከተቻለ ስኬት ላይ እንደሚደረስ አረንጓዴ አሻራ ጉልህ ማሳያ መሆኑን አስታውቀዋል::
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጨምሮ በስንዴ ልማት፣ በሌማት ቱሩፋት፣በገበታ ለሀገር እንዲሁም በአባይ ግድብ ከፍተኛ ስኬት መመዝገቡን አስታውሰው፣ በቀጣይ በሚከናወነው የአረንጓዴ ልማት ላይም መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል:: መድረኩ ለውይይት ክፍት በነበረበት ወቅትም አንዳንድ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት መርሃ ግብሩ የሕዝብ ንቅናቄ የተፈጠረበትና የመንግሥትም ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን መታዘብ መቻላቸውን አስታውቀዋል:: በቀጣይ ለሚከናወነው ልማት ገንቢ ይሆናል ብለው ያሰቧቸውን ሀሳቦችም ሰጥተዋል::
ከተሳታፊዎቹ በስፋት የተነሳው አንዱ አስተያየት የችግኝ ተከላው በጥራት እየተከናወነ አይደለም የሚለው ነው:: ለዚህም ያነሱት ከአካባቢ ሥነምህዳር ጋር ተስማሚ የሆነ ችግኝ አለመምረጥና ሳይንሳዊ የሆነ የአተካከል ዘዴ አለመጠቀም፣ከተተከለ በኋላም ክትትል አለማድረግ የሚሉት ከክፍተቶች መካከል የተጠቀሱ ናቸው፣ ተከላው በዘመቻ መከናወኑም ለጥራቱ መጓደል በምክንያትነት አንስተዋል:: የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖርም ከተነሱት ነጥቦች መካከል ይጠቀሳል::
ከውይይቱ ተሳታፊዎች ከአማራ ክልል የተገኙ ተሳታፊ በሰጡት አስተያየት፤እስካሁን ባለው ተሞክሮ በቅንጅትና በመናበብ ሳይሆን በተናጠል ነው ሥራዎች የሚከናወኑት ሲሉ ተናግረዋል፤ በዚህ ላይ በክልሉ በተደረገ ጥናት በተሰራው ሥራ ልክ ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም ብለዋል:: ለዚህም በቅንጅት የተናበበ ሥራ አለመሥራት አንዱ ምክንያት መሆኑ ተለይቷል ብለዋል:: የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲን በተመለከተ ተሳታፊዋ፤ አማራ ክልል ፖሊሲ እንዳለው ጠቅሰው፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ፖሊሲ ከሌለ በክልሉ ብቻ መኖሩ የሚፈለገውን ውጤት ያስገኛል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል::
ከደቡብ በክልል የተወከሉት ተሳታፊም በተራሮች ላይ የሚከናወን የልማት ሥራ ገና እንደሚቀረው ጠቁመዋል:: በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ቶሎ ደርሶ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኝና ረጅም ጊዜ ወስዶ የሚለማው መለየት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፤ መርሃ ግብሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ አቮካዶ ባሉ የአትክልት ልማት ላይ ትኩረት ማድረጉን በመጥቀስ፣ የደን ልማት ተዘንግቶ መርሃ ግብሩ ዓላማውን እንዳይስት ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል::
ሌላው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምጣታቸውን የገለጹት ተሳታፊ፤የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በንቅናቄ ላይ ያተኮረ መሆኑን በመጠቆም በዚህ መልኩ መቀጠል እንደሌለበት አስታውቀዋል:: ባለቤት ሊኖረው እንደሚገባ ነው የጠቆሙት:: በአስተዳደር የሚመራ የራሱ የሆነ ፋይናንስ እንደሚያስፈልገውም አመልክተዋል:: በዚህ ረገድም ልክ እንደ ገበታ ለሸገር አይነት ገበታ ለደን በሚል ባለሀብቱን የሚያሳትፍ ሥራ ቢሰራም ለዘላቂነቱ ጥቅም እንዳለውም ተናግረዋል::
አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወነ ቢሆንም፣ በምግብ፣ በብዝሀ ሕይወት፣ በውሃ ያስገኘውን ጥቅም በጥናት ማሳየት እንደሚገባ ተሳታፊው ጠቁመው፣ በምርምር ውጤቱን ማሳየት እንደሚገባም አመልክተዋል:: መረጃን አደራጅቶ መያዝ የሚል አስተያየት በሌላ ተሳታፊ ተነስቷል::
ለተነሱት ሀሳቦች የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ በሰጡት ምላሽና ማጠቃለያ፣ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የረጅም ጊዜ ተሞክሮ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ውጤቱና ፋይዳውን ለመሰነድ በ153 ወረዳዎች የጥናት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል:: የጥናቱ ውጤትም በኢኮኖሚ፣ በአካባቢ፣ የአየር ንብረት ለውጥ በመቀነስ እንደሁም በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣በገጠርና በከተማ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ በአጠቃላይ መርሃ ግበሩ ያበረከተውን አስተዋጽኦ የያዘ ሰነድ የማዘጋጀት ሥራ እንደተጠናቀቀ ጠቅሰው፣ የውይይቱ ተሳታፊዎች ለድጋሚ ውይይት እንደሚጋበዙ ገልጸዋል::
ከተሳታፊዎቹ በጉድለት ለተነሱት በተለይም ከጥራት ጋር በተያያዘም ፕሮፌሰሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ ቀደም ሲል ብዛት ላይ ነበር ትኩረቱ፣ አሁን ደግሞ በጥራት ላይ ነው የሚሰራው ሲሉ ገልጸው፣ እሳቸውም ሥራው በዘመቻ መቀጠል አለበት የሚል እምነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል:: ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ አመንጭተዋል:: በጥራት ማስቀጠሉ ላይ እርሳቸው መቸገር የለባቸውም:: አራት አመት ልምድ አግኝተናል:: የጎደለውን ሞልተን ደረጃውን በጠበቀ ሳይንሳዊ በሆነ ሁኔታ መከናወን ይኖርበታል›› ሲሉ ገልጸዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ኃላፊነቱ ወደ ባለሙያዎች እና ምሁራን ይሄዳል::ሀገርንና ትውልድን የሚጠቅም ሥራ መሥራት አንድና ሁለት የሌለው ነገር ነው:: በቅንነት የተጀመረውን ሥራ እያበሰሉ መሄድ ይጠበቃል:: የተከላ ቦታዎችን መምረጥ፣ ለሥነ ምህዳሩ ተስማሚ የሆነ የችግኝ ተከላ ማካሄድ፣ ለደንና ለምግብነት የሚውለውን በመለየት መርሀ ግብሩን በዓላማ ማከናወን የሚጠበቁ ሥራዎች እንደሆኑም አመልክተዋል::
ሶስት ሺ የህብረተሰብ ተፋሰሶች በሶስት ሺ ማህበራት ባለቤትነት የሚመሩ የልማት ሥራዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ፤ በዚህ ረገድ የሚከናወኑ ተግባራትን በመረጃ በማጠናቀር ለምርምርና ለተለያዩ ተግባራት እንዲውሉ በማድረግ እንዲሁም ኢትዮጵያ አቅም የላትም ብለው የተሳሳተ ግምት ለያዙ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጭምር መረጃ የሚያገኙበት ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል:: በተለይም የሚሰራው ሥራ በቁጥር ብቻ ሳይሆን በተግባር በማሳየት ኢትዮጵያ ጀምራ መጨረስ እንደምትችልም በመረጃ ማሳየት ይኖርብናል ብለዋል::
የአረንጓዴ ልማት አጋር ድርጅቶችም ገብተውበት በጀት ተመድቦለት በተቋም እንዲመራ ለማድረግና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የእኔ ነው በሚል ስሜት ተሳትፎው እንዲጎለብትና ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል ሥራዎች እንደሚሰሩም አመልክተዋል:: ከተሳታፊዎች የተነሳው የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ጉዳይና የልቅ ግጦሽ ቁጥጥር ሥርዓት ማበጀትም ትኩረት እንደሚሰጠው ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል:: ፕሮፌሰሩ ተመራማሪዎችና ዓለም አቀፍ የአጋር ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አድርገዋል::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም