ቀደም ባሉት ጊዜያት በእጅ ስራ ከክር ሹራባ፣ ዳንቴል፣ የአልጋ ልብስና የመሳሳሉትን ከመሥራት በዘለለ በዘመናዊ መልኩ ዲዛይን የተደረጉ አልበሳትንና ጫማዎችን መስራት አይስተዋልም ነበር:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከክር የሚሰሩ የእጅ ሥራዎች ውበትን እንዲላበሱ ተደርገው እየተሰሩ ናቸው:: እነዚህ አልባሳት ጠቀሜታቸው እየጎላ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ከመምጣታቸው ባሻገር የዘመኑ ፋሽን እየሆኑ መጥተዋል::
ክርን በመጠቀም በተለመደው መንገድ አልባሳትን በእጅ ከመስራት ባሻገር በተለያዩ አልባሳት ላይ ዲዛይን በማውጣት በዘመናዊ መልኩ ፈጠራ ታክሎባቸው በክር የሚሰሩ የእጅ ሥራዎች የበለጠ ተወዳጅነት እያገኙ የሸማቹን ቀልብ እየገዙት ይገኛሉ:: እነዚህ እዩኝ እዩኝ፤ ልበሱኝ ልበሱኝ የሚሉት የእጅ ሥራዎች በእጅ የሚሰሩ እንደመሆናቸው መጠን ከፍተኛ ጥበብን የሚጠይቁ ናቸው::
የእጅ ሥራ ጥበብን ፈጠራ በማከል ከተለያዩ አልባሳት ጋር በመቀላቀል በተለያየ ቀለምና ዲዛይን ውብና ማራኪ አልባሳትን ማዘጋጀት የዘመኑ ፋሽን ኢንዱስትሪ የሚፈልገው ሆኗል:: ይህ ሥራ በፋሽን ኢንዱስትሪው ጎልቶ እንዲወጣ ለማድረግ ብዙ ጥረት እንደሚጠይቅ ነው በዘርፉ የተሰማራችው ዲዛይነር ቅድስት አበራ የምትናገረው::
ዲዛይነር ቅድስት የእጅ ሥራ ባለሙያ፣ የዲዛይኒንግ ሙያ ባለቤት ናት:: የእጅ ሥራ ሙያን ከልጅነቷ አንስቶ የጀመረችውና ስትጠበብበት የቆየችው ሙያ እንደሆነ የምትናገረው ቅድስት፤ ሙያውን ለማሳደግ ጥረት እያደረገች ትገኛለች::
ቅድስት በህጻናትና የአዋቂ ጫማዎች፣ እስካርፖች፣ ኮፊያዎችና ለብርድ የሚሆኑ የእጅ መሸፈኛ ጓንቶች ላይ የተለያዩ የእጅ ስራ ዲዛይኖችን በመስራት፣ በባህላዊ ልብሶች ላይ የእጅ ሥራዎች በመቀላቀል፤ የሸማ መጋረጃዎችን በመስራት፣ በባህል አልባሳት ላይ የእጅ ሥራዎችን በማስገባት የማስዋብ ሥራዎችን ትሰራለች:: ከዚህ በተጨማሪም የአበባ መትከያዎችን በእጅ ሥራ ማስዋብ፣ የህጻናትና የአዋቂ ሹራቦችን እንዲሁም የህጻናት ቀሚሶች ሙሉ በሙሉ በእጅ እንደምትሰራ ትገልጻለች::
እነዚህ ከክር የሚሰሩ የእጅ ሥራዎችን ለመስራት፣ ኪሮሽና ለሹራብ መስሪያ የሚያገለግሉ ሁለት ሸቦዎች እንዲሁም ጣቶቿን ጭምር ትጠቀማለች:: የእጅ ሥራ ሙያውን ቀደም ሲል ጀምሮ እናቷ ይጠቀሙበት እንደነበር ጠቅሳ፣ እሷም ከሳቸው ተምራ ወደዚህ ሙያ እንደገባች ታስረዳለች::
ክርን በመጠቀም የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ለመስራት መነሻ ሀሳብ የመጣላት ግን ልጅ ወልዳ እቤት በነበረችበት ጊዜ የህጻናት ጫማ ስትሰራ ነበር:: የሰራችውን የህጻናት ጫማ ሰዎች ሲያዩት እንደወደዱትና የአዋቂ ጫማዎችን እንድትሰራ እንደገፋፏት ትናገራለች::
‹‹ከልጅነቴ ጀምሮ የፋሽን ዲዛይኒንግ ሙያ በውስጤ ነበር›› የምትለው ቅድስት፤ የፋሽን ዲዛይኒንግ ሙያዋን ለማሳደግ የሚያስችላትን እውቀት ለማግኘት ስልጠናዎችን መውሰዷን ትናገራለች:: አሁን የምትሰራቸውን አልባሳትንም ሆነ ጫማዎችን ዲዛይን አድርጎ ውበት ሰጥቶ ዘወትር የሚለበሱ ሆነው እንዲቀርቡ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች መሆኑን ታብራራለች::
ምርቶቿን በዲዛይን ሥራዎች ዘመናዊ አድርጋ ስለምትሰራቸው ተቀባይነታቸው እየጨመረ መምጣቱን ነው የምትናገረው:: የእጅ ሥራ በመቀላቀል የምትሰራቸው እነዚህ አልባሳት በፋሽን ኢንዱስትሪው ጎልተው አልወጡም እንጂ ለየት ያለ ውበት ያላቸው ናቸው የምትለው ቅድስት፤ አሁን በተለይ በህብረተሰቡ ዘንድ እየተለመዱ መጥተው የሚፈልጋቸው እየጨመረ ቢሆንም በብዛት ለማምረት የሚያስችላት ሁኔታ ግን የላትም::
ሥራዎቿ ለየት ያሉ ፋሽኖች የተከተሉ በመሆናቸው በህብረተሰቡ በእጅጉ እየተወደዱ እንደሚለበሱም ታስረዳለች:: ልብሶችን በፋሽን ዲዛይን አድርጎ ለመስራት በማሽን እንደምትጠቀም የምትገልጸው ቅድስት፤ ልብሶች ዲዛይን ከሆኑ በኋላ እነሱ ላይ የእጅ ሥራ ለመቀላቀል ስትፈልግ ደግሞ ዲዛይን ያደረገቻቸውን ልብሶች ሰፍታ ስትጨርስ በላያቸው ላይ የእጅ ሥራውን በኬሮሽ ትሰራለች::
ከክር የሚሰሩት የተለያዩ ዲዛይን ያላቸው ጫማዎች የሚመረቱት በማሽን ሳይሆን በሰው ኃይል በእጅ መሆኑን ነው የምትገልጸው:: ለተወሰኑ እናቶች በእጅ ስራ ላይ ስልጠና በመስጠት የተወሰነውን የእጅ ሥራ ሰርተው እንዲሰጧት በማድረግ ቀሪውን የማጠናቀቂያ ሥራ ደግሞ ራሷ እንደምትሰራ ትናገራለች::
አሁን ላይ ለስድስት እናቶች በነጻ ስልጠና በመስጠት የሥራ እድል መፍጠሯን ጠቅሳ፣ በቀጣይ ስልጠና ለመስጠት ደግሞ ተዘጋጅታለች::የእጅ ሥራ ለመስራት ሙያው የሚፈልገው ፍላጎትን ብቻ ነው:: በአጭር ጊዜ ስልጠና ሥራው መስራት የሚችል መሆኑን ተናግራ፣ ፍላጎቱ ያላቸው እናቶችን በማሰልጠን ሙያውን እንዲለምዱት በማድረግ ተደራሽነቱን ለማስፋት ማሰቧን ትናገራለች::
እስካሁን ድረስ ይህንን ሙያ ለማሳደግ በራሷ ጥረት እያደረገች ቢሆንም ድጋፍ የሚያደርግላት አካል እንዳላገኘች የምትናገረው ቅድስት፤ ሙያው ድጋፍ ቢደረግለት ሥራ አጥነት ለመቀነስ እንደሚረዳም ትጠቁማለች:: ‹‹ሙያ አብዛኛውን በእጅ የሚሰራ እንደመሆኑ መጠን እኔ ብቻዬን ብዙ ማምረት አልችልም፤ ስልጠናውን በመስጠት ለሌሎች ማስተላለፍ ቢቻል ብዙ ማምረት እችል ነበር›› ትላለች::
ሥራዎቹ ያላቸው ተቀባይነታቸው ከፍተኛ እንደሆነም ጠቅሳ፣ ምርቱ በሚፈለገው ልክ እንደሌለ አስታውቃለች፤ በብዛት ባለው የሰው ኃይል መስራት ቢቻል ለብዙዎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚቻልም ገልጻለች፤ ስራው እቤታቸው ቁጭ ብለው በቀላሉ መሥራት የሚችሉት እንደሆነም ታብራርለች:: የመንግሥት አካላትም ሆኑ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ለእጅ ስራ ሙያው ትኩረት ሰጥተው ድጋፍ ቢያደርጉ ሙያውን ማሳደግ እንደሚቻልም ጠቁማለች::
በዚህ ሙያ ብዙ መሰልጠን የሚፈልጉ ሰዎች አሉ የምትለው ቅድስት፤ የማሰልጠኛ ቦታ ኖሯት መሰልጠን የሚፈልጉ አካላትን ብታሰለጠን የሥራ እድልም እንደምትፈጥር ጠቁማለች›:: እሷ እንደምትለው፤ ሙያውን ለማስፋፋት ስልጠናዎች በብዛት መስጠት ይኖርባቸዋል፤ ምርቶችም እንዲሁ በብዛት ማምረት አለባቸው፤ ምርቶች የሚታዩበት ማሳያ ቦታዎችም ያስፈልጋሉ፤ እነዚህ ሁሉ ቢሟሉ ሙያውን ማሳደግ ይቻላል::
ቅድስት እንደምትለው፤ እነዚህን ሥራዎቿን ለማስተዋወቅ በግሏ ለሁለት ጊዜያት ያህል በኤግዚብሽኖች ላይ ተሳትፋለች፤ ሥራዎቿን ተደራሽ ለማድረግም የፌስቡክና የቴሌግራም ቻናሎችን ትጠቀማለች:: ከዚህ በተጨማሪም እሷ ዲዛይን ያደረገቻቸውን አልባሳት ከለበሱ ሰዎች በመጠየቅ አንዱ ከአንዱ እየሰማ ሥራዎቿ ሰዎች ዘንድ እየደረሱ እንደሆነ ገልጻለች::
የዚህ ሥራ ተግዳሮት ጫማ ለመስራት የሚያስፈልገው ክር እጥረት በቀላሉ የማይገኙ መሆኑን ጠቅሳ፣ ሲገኝም በየጊዜው የዋጋ ጭማሪ እንደሚያሳይ ጠቁማለች፤ ከጫማው ዲዛይን ጋር የሚሄድ የጫማ ሶል የሚፈለገው የጫማ ቁጥር ላይገኝ እንደሚችልም ትናገራለች:: ውጭ ሀገር የሚኖሩም ሆኑ ሀገር ውስጥ ያሉ ሰዎች ምርቶቿን እንደሚጠቀሙ የምትናገረው ቅድስት፤ ‹ሙያውን በማስፋፋት በዓለም ላይ እንዲተዋወቅ በማድረግ የሀገሯን ስም ለማስጠራት ፍላጎት እንዳላትም ተናግራለች›::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም